አሸባሪው ህወሀት በአማራ ክልል በግብርና ዘርፍ ብቻ ከ266 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረት አውድሟል

58

ደሴ ኢዜአ ታህሳስ 17/2014 (ኢዜአ) 'አሸባሪው የህወሀት ወራሪ ሃይል በአማራ ክልል በግብርና ዘርፍ ብቻ ከ266 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረትና ሀብት ማውደሙን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

'አሸባሪው የህወሀት ወራሪ ሃይል ባደረሰው የኢኮኖሚ ስብራት መቆዘም ሳይሆን በእልህና ቁጭት ጠንከረን መስራትና ማካካስ ከሁላችንም ይጠበቃል'' ሲሉ  በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማእረግ የአማራ ክልል የኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪ ወይዘሮ ዐይናለም ንጉሴ አስገንዝበዋል።

ወይዘሮ ዐይናለም ንጉሴ ከአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የስራ ሀላፊዎች ጋር በመሆን በህወሀት ወራሪ ሀይል የወደመውን የደሴ ቲሹ ካልቸር  በመመልከት በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ሃይለማሪያም ከፍያለው በጋራ መግለጫው እንዳስታወቁት ተስፋ የቆረጠው የህወሀት ወራራ ሃይል ሰብአዊ አገልግሎት የሚሰጡ የግብርናና የጤና ተቋማትን ጭምር በማውደም አረመኔነቱን አስመስክሯል ።

በክልሉ በተደረገ የዳሰሳ ጥናት የአሸባሪው ህወሀት ወራሪ ሀይል የግብርና ኮሌጆችንና መስሪያ ቤቶችን፣ ተሽከርካሪዎችን፣ የሰቆጣ አሳና የላሊበላ ንብ ማዕከሎችን፣ የደሴ ቲሹ ካልቸርንና የመስኖ ፕሮጀክቶችን ጨምሮ አጠቃላይ በግብርናው ዘርፍ ብቻ  ከ266 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት ውድመት ማድረሱን አስታውቀዋል።

"ወቅቱ መኸር ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ከ2 ሚሊዮን ሄክታር የሚበልጥ መሬት ሳይዘራና የለማውም ሰብል ሳይሰበሰብ በመቅረቱ የሽብር ቡድኑ በገባባቸው አካባቢዎች ከ6 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ ህዝብ የራብ አደጋ  አንዣቦበታል" ብለዋል።

"ችግሩን ለማቃለል አንጻራዊ ሰላም በነበረባቸው ዞኖች የለማውን ሰብል ከብክነት ተከላክለን በዘመቻ  ለመሰብሰብ  ጥረት አድርገናል" ብለዋል።

በጦርነቱ የወደመውን 41 ሚሊየን ኩንታል የሚጠጋ ምርትን ለማካካስ አጋጣሚዎችን ሁሉ በመጠቀም በቀሪ እርጥበት፣ በበልግና በመስኖ የተሻለ ምርት ለማግኘት ርብርብ እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።

የክልሉ የኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪ ወይዘሮ ዐይናለም ንጉሴ በበኩላቸው የአሸባሪው ህወሀት ወራሪ ሃይል ያደረሰው ውድመት ክፍለ ኢኮኖሚውን ለበርካታ አመታት ወደ ኋላ የሚጎትትና የታሪክ ጠባሳ የጣለ መሆኑን ተናግረዋል።

አሸባሪው በተለይ የኢኮኖሚው የጀርባ አጥንት በሆነው ግብርና ዘርፍ ላይ የአርሶ አደሩን የእርሻ ማሳሪያ ከመዝረፍ ጀምሮ የመስኖ ፕሮጀክቶችን ጭምር ዳግም እንዳይሰሩ አድርጎ ማውደሙና መዝረፉ ሰብአዊነት የሌለው አረመኔ ስለመሆኑ ያረጋገጠበት ተግባር መሆኑን ጠቅሰዋል።

አሸባሪው የፈፀመው ተግባር ለክልሉ ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያ ኢኮኖሚና በህብረተሰቡ ኑሮ ላይም ከፍተኛ ጫና መፍጠሩን አመልክተዋል።

"የሽብር ቡድኑ ሰብአዊና ቁሳዊ ውድመት የህዝቡን ስነ-ልቦና ክፉኛ ለመጉዳት ቢሞክርም በደረሰው ሁለንተናዊ ውድመት መቆዘም ሳይሆን በየሙያ ዘርፋችን በእልህና በቁጭት ጠንክረን መስራትና ማካካስ ከሁላችንም ይጠበቃል" ሲሉ አስገንዝበዋል።

የወደመውን መልሶ ለማቋቋምና ሁሉንም ተቋሞች በትንሹም ቢሆን ስራ ለማስጀመር የክልሉ መንግሰት ከፌዴራልና ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት በትኩረት እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

"የሽብር ቡድኑ ንጹሃንን በመግደል፣በመዝረፍና ተቋማትን በማውደም የክፋት ጥጉን አሳይቷል'' ያሉት ደግሞ የደሴ ቲሹ ካልቸር ማዕከል ሃላፊ አቶ ሃሰን እንድሪስ ናቸው።

ማዕከሉ በሽታን የሚቋቋሙ፣ ምርታማና በአጭር ጊዜ የሚደርሱ በአመት 20 ሚሊዮን  የቆላና የደጋ ፍራፍሬ እያባዛ ለአርሶ አደሩ የማሰራጨት አቅም ቢኖረውም ሙሉ በሙሉ መውደሙ እንዳሳሰባቸው ገልጸዋል።

በማእከሉ ከውድመትና ዝርፊያ የተረፉና ጉዳት የደረሰባቸው ማሽኖችና የቤተ-ሙከራ መሳሪያዎችን ጠግኖ ስራ ለማስጀመር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

በአሸባሪው ህወሀት ወራሪ ሀይል በአማራ ክልል የደረሰውን ውድመትና ጥፋት በሳይንሳዊ መንገድ በጥናት ለይቶ ለማወቅ በክልሉና በፌደራል መንግስት ትብብር  ስራዎች እየተከናወኑ ስለመሆኑ በጋራ መግለጫው ተመላክቷል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም