"የዳያስፖራው ወደ አገር ቤት ጉዞ ኢትዮጵያን ወደ ገናና ክብሯ የመመለስ ዓላማ አለው"

91

ታህሳስ17/2014/ኢዜአ/ "የኢትዮጵያ ዳያስፖራዎች ኢትዮጵያን ወደ ገናና ክብሯ ለመመለስ አልመው ወደ እናት አገራቸው በመትመም ላይ ናቸው" ሲል የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ተግባር ምክር ቤት ገለጸ።

ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ ለአንድ ሚሊዮን ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵዊያን ያቀረቡትን ጥሪ ተከትሎ በርካታ ቁጥር ያለው ዳያስፖራ ወደ አገር ቤት በመግባት ላይ ነው።

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ተግባር ምክር ቤት የአውሮፓ አስተባባሪ አቶ ዘውዱ መንግስቴ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን አሸባሪው ህወሓትና አንዳንድ ምዕራባዊያን ኢትዮጵያ ላይ የሚያደርሱትን ሁሉን አቀፍ ጫና በመሟገት ላይ መሆናቸውን ለኢዜአ ገልጸዋል።

አሜሪካ ኢትዮጵያን ከአሜሪካ ከቀረጥና ኮታ የገበያ እድል /አጎዋ/ ብታስወጣትም ዳያስፖራው ለአገሩ የሚችለውን ሁሉ ለማድረግ ከተረባረበ የማይሳካ ምንም ነገር የለም ብለዋል።

ዛሬ ማንም የማይደፍራት እስራኤል የተገነባችው በመላው ዓለም ተበትነው በነበሩ እስራኤላዊያን መሆኑን ልብ ማለት ይገባል ነው ያሉት አቶ ዘውዱ።

የኢትዮጵያ የዳያስፖራ የተግባር ምክር ቤት ሊቀመንበር አቶ አለማየሁ አበበ በበኩላቸው "ዳያስፖራዎች ወደ  አገር ቤት ሲገቡ የሕክምና ቁሳቁሶችን በጦርነቱ ለተጎዱ ዜጎችና ለመከላከያ ሠራዊት የሚያደርሱበት 'አንድ ሻንጣ ለወገኔ' የሚል መርሃ ግብር ተዘጋጅቷል" ብለዋል።

ከዚህ ባሻገርም ወደ አገር ቤት የሚገባው ዳያስፖራ በእውቀቱና በገንዘቡ ለአገሩ መልሶ ግንባታ አስተዋጽኦ ለማድረግና ከመንግስት ጎን ሆኖ ለመስራት ማቀዱን አመልክተዋል።

ዳያስፖራው በዲፕሎማሲና በሀብት ማሰባሰብ ዘርፍ ለአገሩ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያደረገ መሆኑን የገለጹት አቶ አለማየሁ፤ "የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ድፍድፍ ነዳጅ ነው" መንግስትም ይህን አቅም ሊጠቀምበት ይገባል ብለዋል።

"ኢትዮጵያ ዘላቂ ኢኮኖሚያዊ ነጻነቷን የምታገኘው በልጆቿ ጥረት እንጂ በአገራት እርዳታ አይደለም" ያሉት ዳያስፖራዎቹ በውጭ ከሚኖረው 3 ሚሊዮን ዳያስፖራ እስከ 4 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር በየዓመቱ መሰብሰብ እንደሚቻል ጠቁመዋል።

ዳያስፖራው አሸባሪዎች ያፈረሱትን መልሶ በመገንባት የኢትዮጵያን ስም ወደ ገናናነቱ የማይመልስበት ምክንያት የለም ብለዋል።

ዳያስፖራው ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ ለመምጣት ብቻ ሳይሆን አገሩን ለመገንባት ቆርጦ መነሳቱንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ተግባር ምክር ቤት በመስከረም 2013 ዓ.ም የተቋቋመ ሲሆን፤ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚገኙ የኢትዮጵያ ዳያስፖራዎችን የያዘ ነው።

ምክር ቤቱ የኢትዮጵያን መልካም ገጽታ በመገንባት፣ በልማትና በትውልድ ቀረጻ ላይ ትኩረቱን አድርጎም የሚሰራ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም