የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል መንግስትና ህዝብ ለአፋር ክልል ተፈናቃዮች ድጋፍ አደረጉ

59

ሰመራ ታህሳስ 17//2014 (ኢዜአ) የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል መንግስትና ሀዝብ በአፋር ክልል በአሸባሪው ህወሓት ለተፈናቀሉ ወገኖች በጥሬ ገንዘብና በአይነት ከ7 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አደረጉ።

የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሐሰን ድጋፉን ለአፋር ክልል ርዕሰ-መስተዳድር አቶ አወል አርባ ዛሬ አስረክበዋል።

ከድጋፉ ውስጥ 5 ሚሊዮን ብር በጥሬ ገንዘብ የተበረከተ ሲሆን ቀሪው ከ2 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው ምግብና ሌሎች የአይነት ድጋፍ ነው።

አቶ አሻድሊ ሐሰን በርክክብ ሥነ ሥርዓት ላይ እንዳሉት የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ሕዝብና መንግሥት በአፋር አሸባሪውና ወራሪው ህወሓት በፈጸመው ጦርነት  ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች ያላቸውን አጋርነት ለማሳየት ድጋፉን አበርክተዋል።

የአፋር ክልል ሕዝብ የአገሩን አንድነትና ሉአላዊነት ለማስከበር ለፈጸመው አኩሪ ጀብድና ለከፈለው መስዋዕነት ከፍተኛ ክብር እንዳለው ገልጸዋል።


ክልሉ በቀጣይም በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸው የመሠረተ-ልማት ተቋማትን መልሶ ለመገንባትና ተጎጂዎችን ለመደገፍ ድርሻውን ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን ርዕሰ መስተዳድሩ አስታውቀዋል።

አቶ አወል አርባ በበኩላቸው የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ሕዝብና መንግሥት ላደረጉት ድጋፍ በክልሉ መንግሥትና ተጎጂዎች ስም ምስጋና አቅርበዋል።

"ኢትዮጵያዊያን ተፈናቃዮችን ለመርዳት የሚያደርጉት ሁለንተናዊ ድጋፍ ጊዜያዊ ችግሮቻችንን ለመሻገር  ያስችለናል" ብለዋል።

በጦርነቱ የፈረሱና የወደሙ ተቋማትን መልሶ ለመገንባትና ተጎጂዎችን ወደቀደመ ኑሯቸው ለመመለስ በሚደረገው ጥረት የሁሉም የዜጎች ድጋፍ እንዳይቋረጥ ርዕሰ መስተዳድሩ ጠይቀዋል።

በአፋር አሸባሪው ህወሓት በፈጸመው ወረራ ከ377ሺህ በላይ ሰዎች ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸውንና
ከ1ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ነዋሪዎች ለችግር መዳረጋቸውን ጠቅሰዋል።

በክልሉ የመንግሥት ተቋማት ላይ  ከ10 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት ውድመት መድረሱንም አቶ አወል አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም