አፍሪካዊያን በኢትዮጵያ ላይ የሚፈጸምን ማንኛውንም ጥቃት አፍሪካ ላይ የተቃጣ አድርገን እንቆጥረዋለን

84

ታህሳስ 17/2014/ኢዜአ/ "እኛ አፍሪካዊያን በኢትዮጵያ ላይ የሚደርስን ማንኛውንም ጥቃት አፍሪካ ላይ እንደተቃጣ አድርገን እንቆጥረዋለን" ይላሉ የኡጋንዳ ብሔራዊ የፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ ሊቀ መንበር ዶክተር ሩጋራማ ዳንኤል ገለጹ።

አፍሪካዊያን የምዕራቡ ዓለም አገራት በአፍሪካ ላይ መጫን የሚፈልጉትን የቅኝ ግዛት አስተሳሰብ እምቢተኝነታቸውን በማሰማት ትግል ማድረግ አለባቸውም ብለዋል።

የኡጋንዳ ብሔራዊ የፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ ሊቀመንበር ዶክተር ሩጋራማ ዳንኤል ኢትዮጵያ በአፍሪካዊያንና በጥቁር ሕዝቦች ዘንድ ትልቅ ቦታ እንዳላት ለኢዜአ ገልጸዋል።

የአፍሪካ አገራት በቅኝ ግዛት ውስጥ በነበሩበት ወቅት ኢትዮጵያ "ነጻነቴን አሳልፌ አልሰጥም" በማለት ባደረገችው ትግል ሉዓላዊነቷን ማስከበር እንደቻለች አንስተዋል።

ኢትዮጵያ ነጻነቷን ለማስጠበቅ ያደረገችው ትግል ለአፍሪካዊያንና ለጥቁር ሕዝቦች ብርታት እንደሰጠና ከጭቆና ለመላቀቅ የተደረገውን እንቅስቃሴ እንዳቀጣጠለ ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅትም ኢትዮጵያ እየተዋጋች ያለችው የውስጥ ጠላቶቿን ብቻ ሳይሆን በእጅ አዙር በአፍሪካ ላይ የቅኝ ግዛት እሳቤን መጫን ከሚሹ ሃይሎች ጋር እንደሆነም አመላክተዋል።

"ኢትዮጵያ በግልጽ የማይታዩ ነገር ግን ከጀርባ ሆነው ኢትዮጵያን በማዳከም አፍሪካን ለማዳከም ከሚንቀሳቀሱ ሃይሎች ጋር እየታገለች ነው፤ ለዚህም ነው ኢትዮጵያ የአፍሪካን ጦርነት እየተዋጋች ነው የምንለው" ብለዋል ዶክተር ሩጋራማ።

ስለዚህም "እኛ አፍሪካዊያን በኢትዮጵያ ምድር ላይ የሚደርሰውን ማንኛውንም አይነት ጥቃት አፍሪካ ላይ የተቃጣ አድርገን እንቆጥረዋለን" ሲሉ ገልጸዋል።

አፍሪካዊያን፣ የፓን አፍሪካኒዝም አቀንቃኞችና ጥቁር ሕዝቦች ከኢትዮጵያ ጎን በመቆም ትግሉን መቀላቀል እንዳለባቸውም አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ የአፍሪካን የነጻነት ትግል በግንባር ቀደምትነት በመምራት በአፍሪካዊያንና በጥቁር ሕዝቦች ዘንድ ያላትን ታሪካዊ ስፍራ ይዛ መቀጠል አለባት ብለዋል።

አፍሪካዊያን የምዕራቡ ዓለም አገራት አፍሪካ ላይ መጫን የሚፈልጉትን የቅኝ ግዛት አስተሳሰብ እምቢተኝነታቸውን በመግለጽ የተደራጀ ትግል ማድረግ ይገባቸዋል ነው ያሉት ዶክተር ሩጋራማ።

አፍሪካ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ ማግኘት አለባት በሚል በነጻነት አባቶቻችን ተጀምሮ አሁን ዳግም የተቀሰቀሰው እንቅስቃሴ አፍሪካዊያን በዓለም መድረክ ፍትሃዊ ውክልና ሊኖራቸው ይገባል የሚለውን ሃሳብ የሚያጠናክር እንደሆነ ገልጸዋል።

"ከአንድ ቢሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት አፍሪካና አፍሪካዊያን  በጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ ሳይኖራት በእርሷ ጉዳይ የሚወሰኑ ውሳኔዎችን እየተቀበሉ መቀጠል የለባቸውም" ብለዋል ሊቀመንበሩ።

አፍሪካዊያን በጋራ በመሆን በምክር ቤቱ መቀመጫ ለማግኘት የተጀመረውን ትግል መቀላቀል እንዳለባቸውም አመልክተዋል።

የአፍሪካ ጥያቄ ተቀባይነት የማያገኝ ከሆነም አፍሪካዊያን የአፍሪካ ሕብረት መዋቅርን ጨምሮ የራሳቸውን ጉዳይ በራሳቸው የሚወስኑባቸው የአሰራር አማራጮችን መከተል እንዳለባቸው አስረድተዋል።

አፍሪካዊያን የጋራ ራዕይና ግብ እንዲኖራቸው፤ የአፍሪካዊነትን ስሜትና መንፈስ በዜጎች ላይ የማስረጽ አስተሳሰብ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራ ይገባልም ብለዋል።

የአስተሳሰብ ነጻነታቸውን ያረጋገጡ የአፍሪካ አገራት በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በሌሎች መስኮች ነጻነታቸውን ለማረጋገጥ እያዳግታቸውም ነው ያሉት ዶክተር ሩጋራማ።

የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና የአፍሪካ አገራትን የእርስ በእርስ ግንኙነት የማጠናከር አቅም አንዳለውና አፍሪካዊያንም ይህን ማዕቀፍ ተጠቅመው የንግድ ግንኙነታቸውን ማጎልበት እንደሚገባቸው ተናግረዋል።

ዶክተር ሩጋራማ የአፍሪካ አገራት በኢኮኖሚ፣ በንግድ፣ በፖለቲካና በሌሎች መስኮች ያላቸውን ትብብር ካጠናከሩ ጠንካራና በራሷ መወሰን የምትችል አፍሪካን መፍጠር እንደሚቻልም አክለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም