የኢትዮጵያዊያን ጠንካራ አንድነት የሽብር ቡድኑን ወረራ መቀልበስ አስችሏል

78

ጎንደር ታህሳስ 17/2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያዊያን ጠንካራ አንድነት ሀገር ለማፍረስ አሰፍስፎ የነበረውን የህወሃት የሽብር ቡድን ወረራን መቀልበስ አስችሏል ሲሉ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር አስታወቁ።

''አብሮነት ለውስጥ ጥንካሬ፣ ለሰላምና ልማት እንዲሁም ለሀገር ህልውና'' በሚል መሪ ሀሳብ የጎንደር የሰላምና የእድገት ማህበር ያዘጋጀው ህዝባዊ የምክክር መድረክ ዛሬ ተካሂዷል፡፡

በመድረኩ የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር ፣የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበልን ጨምሮ የክልል፣ የዞንና የጎንደር ከተማ አመራሮች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ወጣቶች  ተሳትፈዋል፡፡

የፌደሬሽን ምክርት ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር በወቅቱ እንዳሉት በህልውና ዘመቻው የተገኘው ድል የኢትዮጵያውያን የአሸናፊነት ማሳያ ነው፡፡

"ኢትዮጵያውያን በሀገር ሉአላዊነትና አንድነት ላይ የመጣን የውጭም ሆነ የውስጥ ጠላት አንበርክኮና አይቀጡ ቅጣት ቀጥተው ወደ መጣበት የመለሱት ከብረት በጠነከረው አንድነታቸውና የኢትዮጵያዊነት መንፈስ ነው" ሲሉ ተናግረዋል፡፡

"ወራሪው የህወሃት የሽብር ቡድን በደረሰበት ሽንፈት ተቀጥቅጦ ወደ ኋላ ቢያፈገፍግም ወራሪ ሃይሉ የቆመለትን ኢትዮጵያን የማፍረስና ህዝብን የማዋረድ አጀንዳ ለማሳካት ጊዜና ሁኔታ ጠብቆ ዳግም ጥፋት ከመሰንዘር አይቆጠብም" ሲሉም የቡድኑን እኩይ ሴራ አመልክተዋል፡፡

ህዝቡ ዛሬም እንደ ትናንቱ ሊቃጣ ከሚችል ጥቃት ለመከላከልና የአካባቢውን ሰላምና ልማት ለማስጠበቅ እራሱን አደራጅቶ መንቀሳቀስ ግድ የሚልበት ወቅት መሆኑን አስገንዝበዋል።

የጎንደርን የኢንቨስትመንት፣ የቱሪዝምና የልማት እንቅስቃሴዎች ለማሳካት ብሎም የከተማውን ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ ህዝቡ አካባቢውን ነቅቶ በመጠበቅ የጀመረውን ተግባር አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል፡፡

''ኢትዮጵያውያን የኩራታችን ምንጭና እሴቶቻችን የሆኑትን የሀገረ መንግስት፣ የስነ-ጥበብ፣ የሀገር ፍቅርና የጀግንነት ታሪካችን ማስቀጠል ይገባናል'' ያሉት ደግሞ የጎንደር የሰላምና የእድገት ማህበር የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ወርቁ ለምለሙ ናቸው፡፡

"የህወሃት የሽብር ቡድን የቀረጻቸውን የጥፋት ተልእኮ ጨርሶ በማጥፋት በህልውና ዘመቻው የተገኘውን ድል በልማት መድገም ይገባል" ብለዋል።

የህዝቡ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ትኩረት እንዲያገኙና የባህል፣ የቅርስና የታሪክ እሴቶቻችን እንዲጠበቁ ከመንግስትና ከህዝቡ ጋር ማህበሩ በጋራ እንደሚሰራ አስታውቀዋል፡፡

"ኢትዮጵያ ምንጊዜም ቢሆን የጀግኖች መፍለቂያ ሀገር በመሆኑዋ በታሪኳ በጠላት ተደፍራ አታውቅም" ያሉት ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ፍልስፍና ምሁር ዶክተር ዳኛቸው አሰፋ ናቸው።

በምክክር መድረኩ ላይ ጥናታዊ ፁሁፍ ቀርቦ ውይይት ተደርጓል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም