የ"በቃ " ንቅናቄ ዘመቻ ኢትዮጵያዊያን በሀገራቸው ጉዳይ እንደማይደራደሩ ያረጋገጡበት ነው

69

ጂንካ ፤ ታህሳስ 17/2014(ኢዜአ) በውጭና ሀገር ውስጥ በ"በቃ " የንቅናቄ ዘመቻ ኢትዮጵያዊያን ድምጻቸውን በአለም ላይ በማሰማት በሀገራቸው ጉዳይ እንደማይደራደሩ ያረጋገጡበት እውነት መሆኑን ምሁራን ተናገሩ።

ምሁራኑ ለኢዜአ እንዳሉት፤ አንዳንድ ምዕራባዊያን በኢትዮጵያ ላይ የከፈቱትን የእጅ አዙር ጦርነት ለመመከት በየደረጃው የሚገኙ ምሁራን በዲጂታል ዲፕሎማሲው የጀመሩትን ተሳትፎ ማጠናከር ይኖርባቸዋል።

ከምሁራኑ መካከል የጂንካ ዩኒቨርሲቲ የህዝብና አለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ዘርጋው ማንአርጎ በሰጡት አስተያየት ፤ በአንዳንድ የምዕራባዊያን ሀገራት  የሚስተዋለውን የተዛባ አመለካከት እንዲስተካከል እውነታውን ለአለም ህዝብ በማሳወቅ ረገድ  ዲያስፖራዎች ከፍተኛ ሚና መጫወታቸውን ገልጸዋል።

ይህም በተሳሳቱ መረጃዎች በኢትዮጵያ ላይ ተፅዕኖ  ለመፍጠር  የነበሩ  ጫናዎችን ለመከላከል የራሱ አስተዋፅኦ ማድረጉን ጠቅሰዋል።

በተለይ በውጭና ሀገር ውስጥ  በ"በቃ" ንቅናቄ /#Nomore / ዘመቻ  የምዕራባውያን ሀገራት ጣልቃ ገብነትን በመቃወም ድምጻቸውን በአለም ላይ በማሰማት ኢትዮጵያዊን በሀገራቸው ጉዳይ ፍፅሞ እንደማይደራደሩ ያረጋገጡበት  እውነት መሆኑን ተናግረዋል።

የአንዳንድ ምዕራባዊያን ሀገራት ሚዲያዎች በሀገራችን ጉዳይ የሚያሰራጩት የተሳሳተ ዘገባ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን እውነት  የሚቃረን ነው ያሉት ደግሞ  በዩኒቨርሲቲው የጋዜጠኝነትና ተግባቦት መምህር ሀይሬዲን ሙሐመድ ናቸው።

ይህም  አይተው እንዳላየ የሚያልፏቸው እውነታዎች መረጃ በማጣት  ሳይሆን  የራሳቸውን ድብቅ አጀንዳ ለማስፈፀም እንደሆነ ነው ያመለከቱት።

ባለፉት ሳምንታት በበጎ አድራጎት ስራዎች ስለተሳተፉ ተማሪዎች የምዕራባዊያን ሚዲያዎች  የዘገቡበትም መንገድም የድብቅ ሴራቸው ማሳያ ነው ሲሉም ጠቅሰዋል።

አሜሪካን ጨምሮ አንዳንድ የምዕራባዊያን ሀገራት አንዲት ልዑአላዊት ሀገር ላይ የራሳቸውን ፍላጎት ለማስፈፀም ከሚከተሉት ስልት መካከል  ህዝብን ከህዝብ ማጋጨት፣ አማፂያንን  ማደራጀትና መደገፍ  መሆኑን  የተናገሩት ምሁሩ፤ በኢትዮጵያ ላይም ተግባራዊ እያደረጉት ያለው ይህንኑ ነው ብለዋል።

በተለይ ኢትዮጵያ ታላቁን የህዳሴ ግድብ በመገንባት ኢኮኖሚዋን ለማሳደግና እራሷን ለመቻል የምታደርገው ጥረትም በሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም መነሳሳትና የእምቢተኝነት ስሜት ይፈጠራል በሚል ስጋት ኢትዮጵያን ለማዳከም  መነሳሳታቸውን አስረድተዋል።

የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ኩሴ ጉድሼ በበኩላቸው፤  የውጭ ጠላቶች አሸባሪዎችን በመደገፍ በሀገራችን ላይ የከፈቱት የእጅ ዙር  ጦርነት ለመመከት ዲጂታል ዲፕሎማሲው ወሳኝነት አለው ብለዋል።

ይህን ለማጠናከር በተለይ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በዲጂታል ዲፕሎማሲው መስክ በተቀናጀና በተደራጀ አግባብ ተሳትፏቸውን ሊያጎለብቱ እንደሚገባ አመልክተዋል።

አሸባሪው የህወሃት ቡድንን መመከት ስኬታማ አንዲሆን በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚገኙ ዜጎች በ"በቃ" የንቅናቄ ዘመቻ በአንድነት በመሆን ያደረጉት ርብርብ  በዲጂታል ዲፕሎማሲው ትልቅ ውጤት እንዲመዘገብ ማስቻሉን የገለጹት ደግሞ የደቡብ ኦሞ ዞን የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን  ጉዳይ መምሪያ ኃላፊ አቶ መላኩ ለማ ናቸው።

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት  በሀገራችን ጉዳይ ላይ በተደጋጋሚ ባካሄደው ስብሰባ ለውሳኔ መቸገሩ እንዲሁም አንዳንድ ምዕራባውያን ሀገራት በኢትዮጵያ  ጉዳይ  የያዙት የተሳሳተ አቋም መለሳለሱ የዲፕሎማሲያችን ውጤታማነት ማሳያ ነው ብለዋል።

ይህም ተጠናክሮ እንዲቀጥል የሁሉንም ያልተቆጠበ ተሳትፎ ይጠይቃል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም