በአማራ ክልል አሸባሪው ህወሃት በፈጸመው ወረራ የታጣውን የሰብል ምርት ለማካካስ በልዩ ትኩረት እየተሰራ ነው

207

ታህሳስ 16 ቀን 2014 (ኢዜአ) በአማራ ክልል አሸባሪው የህወሃት ቡድን በፈጸመው ወረራ የታጣውን የግብርና ምርት በበጋ የመስኖ ልማት ለማካካስ በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ፡፡

ቢሮው ከውጭ የሚገባ ስንዴ በመስኖ ለመተካት በሚያስችሉና በሌሎች መሰል የግብርና ሥራዎች ላይ ዛሬ በደሴ ከተማ ውይይት አካሂዷል፡፡

የቢሮው ኃላፊ ዶክተር ኃይለማሪያም ከፍያለው እንደገለጹት፤ አሸባሪው ህወሓት አርሶ አደሩ የመኸር ስራውን በሚያከናውንበት ወቅት የፈጸመው ወረራ ችግሩን የከፋ አድርጎታል፡፡

በሚፈለገው ልክ መዝራት እንዳይቻል፣ ለተዘራውም እንክብካቤ እንዳደረግለት እና የደረሰ ሰብልም በአግባቡ እንዳይሰበሰብ ከማድረጉ ባለፈ የአርሶ አደሩን የእርሻ መሳሪያዎችና ንብረት አውድሟል።

“አሸባሪው ቡድን የግብርና ተቋማትን ከመዝረፍ ባለፈ ቢያወድምም መልሶ በማቋቋም ሥራ እንዲጀምሩ በማድረግ የታጣውን ምርት ለማካካስ በቅንጅት እየተሰራ ነው” ብለዋል፡፡

በተለይ ከውጭ የሚገባውን ስንዴ በመስኖ በመተካት የውጭ ጫናውንና የምንዛሬ እጥረትን ለመቀነስ ክልሉ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ኃላፊው አስታውቀዋል፡፡

በዚህ የበጋ ወቅት ከ80 ሺህ ሄክታር የሚበልጥ መሬት በመስኖ ስንዴ ለማልማት ታቅዶ ሥራ መጀመሩን ገልጸው፤ ከ3 ነጥብ 6 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት እየተሰራ እንደሆነ ተናግረዋል።

በመስኖ ልማቱ ከ320 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች የሚሳተፉ ሲሆን 160 ሺህ ኩንታል ማዳበሪያ እና 120 ሺህ ኩንታል ዘር ጥቅም ላይ ይውላል ብለዋል፡፡

ክልሉ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያርግ ጠቁመው፤ በየደረጃው ያለ አመራርና ባለሙያ ልማቱን መደገፍና ውጤታማ ማድረግ እንዳለበት አስገንዝበዋል።

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአማራ ክልል የኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪ ወይዘሮ አይናለም ንጉሴ በበኩላቸውት በሽብር ቡድኑ የተዳከመውን ኢኮኖሚ ለማነቃቃት ሁሉም የድርሻውን መወጣት አለበት ብለዋል፡፡

የወደመውን በመጠገን፣ በማስተካከልና መልሶ በማቋቋም የህዝብ አገልግሎት መስጫ ተቋማትም ወደ ሥራ ለማስገባት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

አርሶ አደሩም መስኖን በዘመናዊ መንገድ በማልማት ምርታማነቱን በማሳደግና ኢኮኖሚውን ማነቃቃት እንዳለበት ጠቁመው፤ “ለዚህም ጠንካራ የቴክኖሎጂና የባለሙያ እገዛ ይደረጋል” ብለዋል።

የደቡብ ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ አሊ ሰይድ፣ በዞኑ በመስኖ ከሚለማው 24 ሺህ ሄክታር ማሳ ውስጥ ከ10 ሺህ ያህሉን በስንዴ ለመሸፈን ቅደመ ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል።

አሸባሪው ህወሓት የአርሶ አደሩን የእርሻ በሬ ጭምር እያረደ ከመብላቱ ባለፈ ለመስኖ ውሃ መሳቢያ የሚጠቀምባቸውን ጀኔሬተሮችንና ሞተር ፓምፖችን ጭምር መዝረፉንና ያልቻለውን ማውደሙን አስታውሰዋል፡፡

በቡድኑ ወረራና ጥፋት  የታጣውን ምርት ለማካካስ ከ1ሺህ ሄክታር የሚበልጥ ማሳ ላይ ስንዴ ለማልማት እየሰሩ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ  የዋግኽምራ ብሔረሰብ ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ደስታዬ ጌታሁን ናቸው፡፡

ዞኑ በአሸባሪው የህወሓት ቡድን በተወረረበት ወቅት የግብርና ተቋሞችን ጨምሮ የእርሻ መሳሪያ ማውደሙን ጠቁመው፣ “መልሰን ለመቋቋም በቅንጅት እንሰራለን” ብለዋል፡፡

የሽብር ቡድኑ በግብርናው ዘርፍ በፈፀመው ውድመት 41 ሚሊዮን ኩንታል የሚገመት የሰብል ምርት ማውደሙን በውይይት መድረኩ ተመልክቷል። 

_ አካባቢህን ጠብቅ፣

_ ወደ ግንባር ዝመት፣

_ መከላከያን ደግፍ።