ሙስናን በመታገል የልማት እቅዶች እንዲሳኩ የምክር ቤቱ አባላት ጠንክረው ሊሰሩ ይገባል

189

ጋምቤላ ፤ታህሳስ 16/2014 (ኢዜአ) ሙስናና ብልሹ አሰራሮችን በመታገል በክልሉ የተጀመሩ የልማትና የመልካም አስተዳደር እቅዶችን እንዲሳኩ የምክር ቤቱ አባላት ጠንክረው ሊሰሩ እንደሚገባ የጋምቤላ ክልል ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አሳሰቡ ።

ለክልሉ ምክር ቤት አባላት በተሻሻለው የአሰራርና የአባላት ስነ-ምግባር ደንብና በሌሎች ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ የአቅም ግንባታ ስልጠና ተሰጥቷል።

የምክር ቤቱ አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ባንቻየሁ ድንገታ በወቅቱ  እንደገለጹት፤ አዲሱ የምክር ቤት አባላት የልማት ማነቆ የሆኑትን ሙስናና ብልሹ አሰራሮችን በመታገል እንደ ሀገር የተጀመረውን የልማትና የብልጽግና ጉዞ ዳር ለማድረስ  በትጋት መስራት ይጠበቅባቸዋል።

በተለይም ባለፉት ዓመታት በህዝብ ሲነሱ የቆዩ ቁልፍ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ምላሽ ለመስጠት የምክር ቤት አባላት የመረጣቸው ህዝብ ድምጽ በማክበር ተግተው ሊሰሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ምክር ቤቱ የተሰጠውን ስልጣንና ተግባር በመጠቀም የታቀዱ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎችን በመከታተልና በመቆጣጠር ውጤታማ እንዲሆኑ በማድረግ ረገድ ከምክር ቤቱ አባላት የላቀ ቁርጠኝነት እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።

ስልጠናው የምክር ቤት አባላት የተሰጣቸውን ስልጣንና ተግባር በመገንዘብ  ኃላፊነታቸውን በብቃት እንዲወጡ ለማስቻል መሆኑንም ገልጸዋል።

ከምክር ቤቱ አባላት መካከል አቶ አለማየው ዋይዋይ በሰጡት አስተያየት፤ በክልሉ ህዝብ ሲነሱ የነበሩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

የክልሉ ህዝብ ባለፉት 27 ዓመታት በአሸባሪው የህወሃት ቡድን ሀብቱን ከመዘረፍና ሰላሙን ከማጣት ባለፈ የልማት ተጠቃሚ ሳይሆን መቆየቱን አስታውሰው፤ ባለፉት ዓመታት በክልሉ የታጣውን ልማት ለማካካስ ጠንክረው እንደሚሰሩ አስታውቀዋል።

የአቅም ግንባታ ስልጠናው የተሰጣቸውን ተግባርና ኃላፊነት በብቃት ለመወጣት እንደሚያግዛቸውም ነው የገለጹት።

በክልሉ ባለፉት ዓመታት በህወሓት ዘዋሪነት ሲካሄዱ የቆዩትን የሙስና ብልሹ አሰራር ችግሮች በማስቀረት ለክልሉ ዘላቂ ሰላምና ልማት በትጋት ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ ሌላው የምክር ቤቱ አባል አቶ ፍጹም ብርሃኑ ናቸው።

የአቅም ግንባታ ስልጠናው በህዝብ የተጣለባቸውን ተግባርና ኃላፊነት በአግባቡ ለመወጣት አቅም እንደሚፈጥርላቸው ተናግረዋል።