አፍሪካዊያን በኢትዮጵያ ላይ የተቃጣውን የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ በተደራጀ አግባብ ሊገቱት ይገባል…ምሁራን

169

ሚዛን፣   ታኅሣሥ 16/2014 (ኢዜአ) አፍሪካዊያን በኢትዮጵያ ላይ የተቃጣውን የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ በተደራጀ አግባብ የበቃን ትግል በመደገፍ ሊገቱት እንደሚገባ የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርስቲ ምሁራን አስታወቁ።

አንዳንድ ምዕራባውያን ሀገራት አፍሪካን በበላይነት በመቆጣጠር ሀብቷን በመዝረፍ በድህነት እንድትማቅቅ ሲያደርጉ የቆዩ መሆኑን ምሁራኑ ለኢዜአ ተናግረዋል።

ይህንን ፈፅሞ ያልተቀበለችውና ወደ ፊትም የማትቀበለው ኢትዮጵያ ዛሬም እንደ ትላንቱ የአንዳንድ ምዕራባውያንን የጭቆና ቀንበር በቃ በማለት ከራሷ ባለፈ ስለ አፍሪካ ነፃነት እየታገለች መሆኗን  በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርስቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህር አቶ ሳምሶን ወልዴ  ተናግረዋል።

“አንዳንድ ምዕራባውያን  በአፍሪካ ሀገራት ጠንካራና በህዝብ የሚወደድ መንግስት እንዲኖር አይፈልጉም” ያሉት አቶ ሳምሶን ፤ ይልቁንም  እንዳሻቸው የሚያዙት ተላላኪ መንግሥታት ለማስቀመጥ የማይምሱት ጉድጓድ እንደሌለ አመልክተዋል።

ይህን ተቀባይነት የሌለው  እሳቤያቸውን በኃይል ለመጫን በማለም በኢትዮጵያ ህዝብ ይሁንታ አግኝቶ የተመሰረተን መንግስት በተለያዩ ተዕኖዎች ለማፍረስ ከአሸባሪው የህወሓት ቡድን ጋር በመመሳጠር እየሰሩ መሆናቸውን የሚያሳዩ ይፋ የወጡ በርካታ መረጃዎች እንዳሉ ጠቅሰዋል ።

ተጽእኖውን ለመቀልበስ በሀገር ውስጥ እየተካሄደ ካለው ትግል ጎን ለጎን በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን እያሰሙት ያለው #Nomore /የበቃ ንቅናቄ በመቀላቀል ረገድ አፍሪካዊያን ያሳዩት በጎ ምላሽ የሚደነቅ መሆኑን ገልጸዋል።

በአሜሪካና በአንዳንድ ምእራባዊያን ሀገራት የተጠነሰሰውን  የነጻነት ቅሚያ መላው አፍሪካውያን በጋራ ከመቃወም ባለፈ የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝን በተደራጀ አግባብ በመታገል ሊገቱት እንደሚገባ ጠቁመዋል።

አሁን ላይ የበቃ ዘመቻ ወደ ንቅናቄ ተቀይሮ የፓንአፍሪካኒዝም ቅርጽ መያዙን ጠቅሰው፤ ይህንን ንቅናቄ በማቀጣጠል የአፍሪካዊያንን  ዘላቂ ነጻነት  በገሀድ ማረጋገጥ እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል ።

“ባሳለፍነው ሳምንት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ያካሄደውን ልዩ ስብሰባ የአፍሪካ ሀገራት መቃወማቸው  የኢትዮጵያ ጉዳይ የአፍሪካ ጉዳይ እየሆነ ስለመምጣቱ ማሳያ ነው” ሲሉ መምህር ሳምሶን አስታውቀዋል።

በዩኒቨርስቲው የሰላምና ደህንነት መምህር ረዳት ፕሮፌሰር ታገል ወንድሙ በበኩላቸው  የነጻነት ዓርማ የሆነችው ኢትዮጵያ ነጻነቷ እንዳይነጠቅ የአፍሪካ ሀገራት በተደራጀ አግባብ መታገል እንዳለባቸው ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የገጠማትን ፈተናና የአንዳንድ ምዕራባውያን ጫና በራስ ልክ ተመልክተው  ለመፍረድ እንደ አፍሪካ ሀገራት የሚቀርብ እንደሌለ ጠቅሰው፤ አፍሪካ ህብረትም ትግሉን በይፋ መደገፍ እንደሚገባው አመልክተዋል ።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በበቃ ንቅናቄ  የኢትዮጵያ ጉዳይ የአፍሪካውያን ጉዳይ ተደርጎ ቅቡልነት እያገኘ መምጣቱ  ለቀጣይ ትግል መልካም አጋጣሚ እንደሚፈጥርም አስረድተዋል።

አፍሪካ ከየትኛውም አህጉር ያላነሰ ሀብትና የሰው ኃይል እንዳላት እየታወቀ በልማትና በእርዳታ ሰበብ አንዳንድ ምእራባዊያን ሀገራት በውስጥ ጉዳይ ጣልቃ እየገቡ ድህነትንና ዘመናዊ ባርነትን ለማስፋፋት የሚያደርጉት እንቅስቃሴ እንዲቆም ሁሉም አፍሪካዊ መታገል እንዳለበት ነው መምህር ታገል ያስገነዘቡት።