ዳያስፖራዎች ምቹ ጊዜ እንዲያሳልፉ ለማስቻል የደቡብ ክልል ተሰናድቷል

69

ሀዋሳ፣ ታህሳስ 16 ቀን 2014 (ኢዜአ) ለገና በዓል ሀገር ቤት የሚገቡ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በደቡብ ክልል ምቹ ጊዜ እንዲያሳልፉና የኢንቨስትመንት አማራጮች እንዲመለከቱ ለማስቻል ዝግጅት መደረጉ ተገለጸ ።

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊ አቶ ሃይለማሪያም ተስፋዬ፤ ዳያስፖራው ወደክልሉ ሲመጣ መልካም ጊዜ እንዲያሳልፍ የመስህብ ስፍራዎችን በአግባቡ ለማስተዋወቅ የሚያስችል አሰራር ተዘርግቷል ።

አዲስ አበባን መነሻ በማድረግ በተሽከርካሪና አውሮፕላን ለሚጠቀሙ ሶስት አማራጮችና መግቢያ መንገዶች መመረጣቸውን አስረድተዋል።

ከአዲስ አበባ በተሽከርካሪ  የሚመጡ እንግዶች ከጉራጌ ዞን ጢያ ትክል ድንጋይ በመነሳት ስልጤ፣ ሀዲያ፣ ካምባታ ጣምባሮ፣ ሀላባ፣ ወላይታ እና ጋሞ ዞን በማድረግ ኮንሶና ደቡብ ኦሞ የሚገኙ ሃይማኖታዊ ቦታዎች፣ የተለያዩ ማህበረሰብ ጨዋታዎችና ቅርሶች እንዲጎበኙ ሁኔታዎች መመቻቸታቸውን ገልጸዋል።

አውሮፕላን የሚጠቀሙ ደግሞ አርባ ምንጭና ጂንካ በረራ በማድረግ አካባቢው ላይ የሚገኙ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ መስህቦች እንዲመለከቱ ለማድረግ የሚያስችል አሰራር መዘርጋቱን አብራርተዋል ።

በካምባታ ጣምባሮ ዞን የሚገኘው 777 የአምባርቾ ተራራና አጆራ ፏፏቴን፣ የአርባምንጭ የአዞ እርባታ ማዕከል፣ የአባያና ጫሞ ሃይቆች መሳጭ ተፈጥሮዊ መስህቦችን መጎበኘት የሚገባቸው መሆኑን ጠቅሰዋል።

በክልሉ የሚገኙ አምስት ብሄራዊ ፓርኮች፣ የኮንሶ፣ በደቡብ ኦሞ የሚገኙ የ16ቱ ብሄረሰቦች ባህላዊ ጨዋታዎች ጨምሮ በዳያስፖራው ለማስተዋወቅ እየተዘጋጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በተለይ ዳያስፖራው በርከት ብሎ በሚገባባቸው ቀናት በመለየት በአርባምንጭና ጂንካ ባህላዊ ዕሴቶች ለማስተዋወቅና በቂ ግንዛቤ እንዲኖረው ለማስቻል የባህል ፈስቲቫል ለማዘጋጀት ታቅዷል።

በክልሉ የሚገኙ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት 30 በመቶ የዋጋ ቅናሽ እንዲያደርጉ መግባባት ላይ የተደረሰ መሆኑን የተናገሩት ሃላፊው፤ በተለይም ባለኮከብ ሆቴሎችና ሪዞርቶች ምቹና ሳቢ ከመሆን ባለፈ ባህላዊ ትውፊቶችን በማስቀመጥ የሚጠበቅባቸውን ሃላፊነት ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አስታውቀዋል ።

የጎበኚዎች ደህንነት ለመጠበቅ በክልሉ በሁሉም አከባቢዎች የሚገኙ የጸጥታ መዋቅሮች በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል ።

በክልሉ የኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ቢሮ የኢንቨስትመንትና ዳያስፖራ ዘርፍ ምክትል ቢሮ ሃላፊ አቶ ደምሰው ባቾሬ በበኩላቸው፤ ወደ ክልሉ የሚመጡ ዲያስፖራዎች የኢንቨስትመንት አማራጮች እንዲመለከቱ የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ ነው ብለዋል ።

እያንዳንዱ ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች የኢንቨስትመንት ዕምቅ አቅም እንዳላቸው ለዳያስፖራው ያስተዋውቃሉ ብለዋል።

_ አካባቢህን ጠብቅ፣

_ ወደ ግንባር ዝመት፣

_ መከላከያን ደግፍ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም