የኪነ ጥበብና ዕደ ጥበበ ዘርፉ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት የድርሻውን እንዲያበረክት እየተሰራ ነው

239

አዳማ፣ ታህሳስ 16/2014 (ኢዜአ )-የኪነ ጥበብና ዕደ ጥበበ ዘርፍ ተገቢውን ትኩረት አገኝቶ በሀገሪቷ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ውስጥ የራሱን ድርሻ እንዲያበረክት እየሰራ መሆኑን የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሚኒስቴሩ ለዘርፉ አመራሮች፣ ባለሙያዎችና ባለድርሻ አካላት በሴክተሩ በፖሊስና ህግ ማዕቀፎች ላይ ያዘጋጀው የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ዛሬ በአዳማ እየተካሄደ ነው።

የባህልና ስፖርት ሚኒስትር አቶ ቀጄላ መርዳሳ በወቅቱ እንደገለጹት በሀገሪቱ የኪነ ጥበብና ዕደ ጥበብ እንዲሁም የፈጠራ ስራዎች ተገቢውን ትኩረት አላገኙም ።

“ዘርፉ በኢትዮጵያ ባህልና ገፅታ ግንባታ ውስጥ ከዚህ በፊት ቦታ እንዲኖረው አልተደረገም፣ ቦታም አላገኘም፣ ለዚህ ትልቁ ምክንያት በመንግስት ተገቢውን ትኩረት ያለማግኘቱ ነው” ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት መንግስት ዘርፍ ተገቢውን ትኩረት አገኝቶና በሀገሪቱ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማትና እድገት  ውስጥ የራሱን ድርሻ እንዲያበረክት ፖሊሲና የህግ ማእቀፎችን ቀርፆ ወደ ስራ መግባቱን ተናግረዋል።

በሀገሪቱ የኪነ ጥበብ፣ እደ ጥበብና የፈጠራ ስራዎችን ማሳደግ የመንግስት አንዱ አቅጣጫ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ ገፅታ ግንባታ፣ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማትና ዕድገት ብሎም በፖለቲካው መስክ ጭምር ሚና እንዲኖራቸው እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

“በተለይ በመፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ለመገንባት ዘርፉ የላቀ ሚና አለው” ያሉት አቶ ቀጄላ ሁሉንም ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦችን ተደራሽ ያደረጉ ትርጉም ያላቸው ስራዎች መስራት ይጠበቅብናል” ብለዋል።

“ኪነ ጥበብና እድ ጥበብ  የህዝብ ለህዝብ ግኑኝነት እንዲጠናከርና ህብረ ብሔራዊ አንድነት እንዲጎለብት ሚናቸው የጎላ ነው” ያሉት ደግሞ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ነፊሳ አልማሃዲ ናቸው።

“ባለፉት 27 ዓመታት ለኪነ ጥበብ፣ እደ ጥበብና የፈጠራ ልማት ስራዎች ትኩረት አልተሰጠም” ያሉት ወይዘሮ ነፊሳ አሁን ላይ ዘርፉን ለማልማትና ለማሳደግ የፖሊስና የህግ ማእቀፎች ከማሻሻል ጀምሮ የአሰራር ስርዓት በመዘርጋት ወደ ተጨባጭ ስራ መገባቱን አመልክተዋል።

በተለይ የሀገሪቱን ባህላዊ እሴቶች በመጤ የውጭ ተፅዕኖ ስር እንዳይወድቅ በሴክተሩ ልማትና እድገት ላይ ሁሉም የባለድርሻ አካላት ጥረት አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።

“ሀገሪቱን ፈጥነን ከድህነትና ኋላቀርነት ለማላቀቅ እምቅ ሀብታችን በሆነው የኪነ ጥበብና እደ ጥበብ ላይ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ታግዘን መስራት ስንችል ነው” ያሉት ደግሞ በመድረኩ ላይ ፁሑፍ ያቀረቡት ዶክተር ተስፋ ወርቅነህ ናቸው።

“በተለይ የዕደ ጥበብ ስራው በቴክኖሎጅ መደገፍና አመች የሆኑ አሰራሮችን በመዘርጋት በርካታ ዜጎች በዘርፉ ልማትና እድገት እንዲሰማሩ ማድረግ አለብን” ብለዋል።