በአምቦ ከተማ አንድ ባለሀብት በ15 ሚሊዮን ብር ያስገነቡት አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተመረቀ

154

አምቦ ፤ታህሳስ 16/2014 (ኢዜአ) በአምቦ ከተማ አንድ ባለሃብት በ15 ሚሊየን ብር ወጪ ያስገነቡት የአምቦ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ጀመረ።

የኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ ምክትል ሃላፊ ዶክተር ገላና ወልደሚካእል ትምህርት ቤቱን ዛሬ መርቀው ስራ አስጀምረዋል ።

የትምህርት ቤቱ ዳይሬክተር ወይዘሮ ጣይቱ ጫላ ለትምህርት ቤቱ ግንባታ ባለሀብት አቶ ሻቃ ጉርሜሳ ከ15 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ ማድረጋቸውን በስነ ስርአቱ ላይ ተናግረዋል።

የትምህርት ቤቱ ግንባታ በአራት ወራት ጊዜ መጠናቀቁን ጠቁመው ባሉት አራት ብሎኮችና 16  የመማሪያ ክፍሎች 900 ተማሪዎቹን የማስተናገድ አቅም እንዳለው አስታውቀዋል ።

ትምህርት ቤቱ በ1975 ዓም ከአፈር የተሰራ በመሆኑ በእርጅና ምክንያት የመፍረስ አደጋ ተጋርጦበት እንደነበር ጠቁመው ባለሃብቱ ቀድሞ የተማሩበትን ትምህርት ቤት ቃል በገቡት መሰረት ገንብተው በማስረከባቸው ምስጋና አቅርበዋል ።

የአምቦ ከተማ አስተዳደር ካንቲባ አቶ ሃጫሉ ገመቹ  ትምህርት ቤቱ በማርጀቱ ለመማርና ማስተማር ምቹ ስፍራ እንዳልነበር አስታውሰው ደረጃውን በጠበቀ መልኩ በመገንባቱ ምሰጋና አቅርበዋል ።

በክብር እንግድነት የተገኙት የኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ዶክተር ገላና ወልደሚካእል በበኩላቸው "የትምህርት ቤቱ ግንባታን ልዩ የሚያደርገው በታቀደለት ጊዜ ገደብ መጠናቀቁ ነው" ብለዋል።

"የፈረሰውን ትምህርት ቤት ሙሉ በሙሉ አፍርሶ በአዲስ መስራት ትውልድ የማይረሳው ውለታ በመሆኑ ባለሀብቱ ምስጋና ይገባቸዋል" ሲሉ እውቅና ሰጥተዋል።

"ሀገር የምትለወጠው በትምህርት ነው" ያሉት ዶክተር ገላና ሌሎችም ባለሀብቶች ዘርፉን እንዲደግፉ ጠይቀዋል ።

በትምህርት ቤቱ ለ20 አመታት ያስተማሩት መምህር አበበ ሻምቢ ትምህርት ቤቱ በእርጅና ምክንያት በመፍረሱ በመማር ማስተማር ሂደቱ ከፍተኛ ችግር እየፈጠረ እንደነበር አስታውሰው  በአዲስ መልክ በመገንባቱ መደሰታቸውን ገልጸዋል፡፡

"ትምህርት ቤቱ በማርጀቱ በአቧራ አይናችን ይታመም ነበር፤  አሁን ዘመናዊ ትምህርት ቤት ስለተገነባልን ደስ ብሎኛል " ያለው ደግሞ  የአምስተኛ ክፍል ተማሪ ሞሲሳ ቀልቤሳ ነው።

በምርቃ ስነስርአት ላይ  የክልሉ የዞንና የከተማ አስተዳደር አመራሮች፣ የተማሪዎች ቤተሰቦችና ተማሪዎች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው  እንግዶች ተገኝተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም