የሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ ለዳያስፖራዎችን የመዝናኛና የመስተንግዶ ፕሮግራም አዘጋጅቷል

221

ጎንደር ፤ ታህሳስ 16/2014(ኢዜአ) በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ ወደ ሀገር ቤት ለሚገቡ ዳያስፖራዎች የመዝናኛና የመስተንግዶ ፕሮግራም ማዘጋጀቱን የሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

የጽህፈት ቤቱ ሃላፊ አቶ አበባው አዛናው ለኢዜአ እንደተናገሩት የዲያስፖራው ወደ ሀገር ቤት መግባት ተቀዛቅዞ የቆየውን የፓርኩን የቱሪስት ፍሰት ለመጨመር የላቅ አስተዋጽኦ አለው፡፡

ፓርኩን ለመጎብኘት ወደ አካባቢው ለሚመጡ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ምቹ የጉብኝት ጊዜ እንዲኖራቸው ለማድረግ የሚያስችሉ ዝግጅቶች መደረጋቸውን ገልፀዋል።

ለዚህም የጎብኝዎችን ቀልብ የሚይዙና የቆይታ ጊዜያቸውን የሚያራዝሙበት የመዝናኛና የመስተንግዶ ፕሮግራሞች መዘጋጀታቸውን አመልክተዋል።

በተለይ በፓርኩ የሚገኙ ብርቅዬ የዱር እንስሳት ዋልያ፣ ቀይ በሮና የጭላዳ ዝንጀሮ መኖሪያ ስፍራዎችን ዳያስፖራዎች በቀላሉ በአካል ለመመልከት የሚችሉባቸው ሁኔታዎች መመቻቸታቸውን ተናግረዋል፡፡

በአፍሪካ በከፍታው የሚታወቀውን የራስ ዳሽን ተራራ በእግር የመውጣት ፕሮግራም ለጎብኚዎች ስለመሰናዳቱም እንዲሁ፡፡

በፓርኩ ክልል ውስጥ የሚገኙ የቱሪስት ማረፊያዎች፣ ማደሪያ ካምፖችና ንጹህ አየር መቀበያ ስፍራዎችን ጥገናና እድሳት በማድረግ ለጎብኚዎች ምቹ የማድረግ ስራዎችም እየተከናወኑ ናቸው ብለዋል፡፡

የፓርኩን ክልል ጽዳት ከመጠበቅ ጀምሮ የንጹህ መጠጥ ውሃ አገልግሎት የሚሰጡ መሰረተ ልማቶች የተሟላ አገልግሎት የሚሰጡበት ሁኔታ መመቻቸቱን አስታውቀዋል፡፡

የህወሃት የሽብር ቡድን በፓርኩ መሰረተ ልማትና ብርቅዬ የዱር እንስሳቶች ላይ ጉዳት ለመፈጸም ከዚህ በፊት ያደረገው ሙከራ በጀግኖች የፀጥታ ሃይሎች ተጋድሎ በመክሸፉ የፓርኩን ደህንነት ማስጠበቅ መቻሉን አውስተዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በአካባቢው አስተማማኝ ሰላም ከመኖሩም በላይ ህዝቡ የፓርኩን ደህነንት ለማስጠበቅ ከምንጊዜውም በላይ አካባቢውን በንቃት በመጠበቅ እየተሳተፈ እንደሚገኝም አስረድተዋል፡፡

”የዳያስፖራው ወደ ሀገር ቤት ጥሪው በራሱ ከቱሪዝም ገቢው ተጠቃሚ የሆነውን የፓርኩን ክልል ህብረተሰብ ያነሳሳ ነው” ያሉት የደባርቅ ከተማ የኢኮ ቱሪዝም ማህበር ሊቀ መንበር አቶ ሞገስ አየነው ናቸው፡፡

ማህበሩ ፓርኩን ለመጎብኘት ወደ አካባቢው የሚመጡ ዳያስፖራዎችን ለማስተናገድ ዝግጁ መሆኑን ጠቁመው፤ በተለይም የጎብኚዎችን ጓዝ በመጫን ፣በቅሎ በማከራየትና መንገድ በመምራት አገልግሎት ይሰጣል ብለዋል፡፡

ቁጥራቸው 8 ሺህ የሚደርሰው የማህበሩ አባላት በኢትዮጵያዊ ባህልና ወግ እንግዶቹን ተቀብሎ ለማስተናገድ በጉጉት እየጠበቀ እንደሚገኝም ሊቀ መንበሩ ተናግረዋል፡፡

እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ1978 በተባበሩት መንግስታት የትምህርት የሳይንስና የባህል ድርጅት /ዩኔስኮ/ በአለም የተፈጥሮ ቅርስነት የተመዘገበው ፓርኩ 412 ስኩየር ኪሎ ሜትር ስፋት አለው፡፡

በማራኪና ድንቅ የተፈጥሮ አቀማመጥ የታደለው የሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙትን ዋልያ፣ ቀይ ቀበሮና ጭላዳ ዝንጀሮን ጨምሮ የተለያዩ የብርቅዬ የዱር እንስሳትና አእዋፋት መገኛ ስፍራ ነው፡፡