በክልሉ ከህወሃት ወረራ ነጻ በወጡ አካባቢዎች ለሚገኙ ወገኖች በየወሩ 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል እህል ያስፈልጋል

58

ባህር ዳር፣  ታህሳስ 16/2014(ኢዜአ) በአማራ ክልል አሸባሪው ህወሓት በወረራ በቆየባቸው አካባቢዎች ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች በየወሩ 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል የምግብ እህል እንደሚያስፈልግ የክልሉ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ኮሚሽን አስታወቀ።

ኮሚሽነሩ አቶ ዘላለም ልጃለም ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ እንዳሉት አሸባሪው ህወሓት በክልሉ በወረራ ይዟቸው በቆዩ ሰባት ዞኖች ከፍተኛ የሆነ ሰብዓዊና ቁሳዊ ውድመት አድርሷል።

በዶክተር ዐቢይ ጥሪ መሰረት የገና እና የጥምቀት በዓልን ለማክበር ወደ አገር ቤት የሚመጡ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ወገኖችን በማወያየትና በክልሉ ጉዳት የደረሰባቸውን አካባቢዎች እንዲመለከቱ በማድረግ በመልሶ ማቋቋምሥራው የራሳቸውን አሻራ እንዲያሳርፉ እንደሚደረግ አስታውቀዋል።

በወረራ ተይዘው በቆዩ አካባቢዎች ለሚኖሩ 11 ነጥብ 4 ሚሊዮን ዜጎች በአሁኑ ወቅት በየወሩ 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል የምግብ እህል ማቅረብ እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል።

"የምግብ እህል የሚያስፈልጋቸው ዜጎች የአሸባሪውን ህወሓት ጭቆናን ተቋቁመው አካባቢያቸውን ሳይለቁ የቆዩ እና ተፈናቅለው ቆይተው አሁን ወደ ቀያቸው እየተመለሱ ያሉ ናቸው" ብለዋል።

እንደ ኮሚሽነሩ ገለጻ የሽብር ቡድኑ ለአምስት ወራት በወረራ ሲቆይ  ቀያቸውን ያልለቀቁ 9 ነጥብ 1 ሚሊዮን ዜጎች በስቃይ ውስጥ መቆየታቸውን አስታውሰዋል።

እነዚሁ ዜጎች ምንም አይነት የእርዳታ እህል ድጋፍ ከአንድም ዓለም አቀፍ ድርጅት ባለማግኘታቸው ለከፋ ርሃብ ተዳርገው እንደቆዩ ተናግረዋል።

ከቀያቸው ተፈናቅለው በሰባት መጠለያ ጣቢያዎችና በዘመድ አዝማድ ተጠልለው ለቆዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ግን አቅም በፈቀደ ድጋፍ ሲደረግላቸው መቆየቱን አመልክተዋል።

ወደ ቀያቸው እየተመለሱ ለሚገኙም ሆነ አካባቢያቸውን ሳይለቁ ለቆዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በአሁኑ ወቅት ከ70 ሺህ ኩንታል በላይ የምግብ እህል እየተከፋፋለ መሆኑን ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።

ተጎጂዎችን መልሶ ለማቋቋም በሚደረገው ሂደት መንግስት፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ ህብረተሰቡ፣ ባለሀብቱና መላው የኢትዮጵያ ህዝብና ወዳጆች ሁሉን አቀፍ ድጋፍ እንዲያደርጉ አቶ ዘላለም ጥሪ አቅርበዋል።

ኮሚሽኑ የተፈናቀሉ ወገኖችን ወደ ቀያቸው ለመመለስ በጀመረው ሥራ እስካሁን ድረስ ከ313 ሺህ በላይ ዜጎች መመለሳቸው  ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም