አሜሪካ በሚኖሩ ኢትዮጵያዊ ድጋፍ የግንባታ ማሻሻያ የተደረገለት ትምህርት ቤት ለአገልግሎት በቃ

277

ጎንደር፤ ታህሳስ 16/2014(ኢዜአ) በጎንደር ዙሪያ ወረዳ የሚገኘው የማክሰኝት አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አሜሪካ በሚኖሩት ዶክተር አስረሱ ምስክርና ቤተሰቦቻቸው ባደረጉት ድጋፍ የማሻሻያ ግንባታው ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ጀመረ።

ትምህርት ቤቱ ላለፉት 54 ዓመታት ምንም የግንባታ ማሻሻያ ያልተደረገለት ሲሆን የማሻሻያ ግንባታው ከደረጃ በታች የነበረውን ትምህርት ቤት ደረጃው እንዲሻሻል እንደሚያስችልም ተገልጿል።

በትምህርት ቤቱ የተገነቡት ስድስት ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎችም ከ700 በላይ ተማሪዎችን በሁለት ፈረቃ ማስተናገድ እንደሚያስቸሉ ተጠቁሟል።

በዚህ ወቅት ዶክተር አሰረሱ እንዳሉት፤ ብቁና የተማረ ዜጋ ለማፍራት ደረጃቸውን የጠበቁ ትምህርት ቤቶች ያስፈልጋሉ።

“እኔና ቤተሰቦቼ ሳይማር ላስተማረኝ ወገኔ የአቅሜን ማበርከት አለብኝ በሚል ተነሳስተን ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ ለትምህርት ቤቱ መሻሻል የአቅማችንን አበርክተናል” ብለዋል፡፡

በትምህርት ቤቱ ተማሪዎች የሙያ ባለቤት እንዲሆኑ በቀጣይ ወርክ ሾፕ እና ደረጃውን የጠበቀ ቤተ-መጻፍት ገንብተው ለማስረከብም ዶክተር አስረሱ ቃል ገብተዋል፡፡

የጎንደር ዙሪያ ወረዳ ትምህርት ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አጠቃ መኮንን እንዳሉት በሀገር ወዳድ ዳያስፖራ በትምህርት ቤቱ የተገነቡት ስድስት ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎች ከ700 በላይ ተማሪዎችን በሁለት ፈረቃ ማስተናገድ ያስቻሉ ናቸው ብለዋል።

ትምህርት ቤቱ ላለፉት 54 ዓመታት ምንም የግንባታ ማሻሻያ እንዳልተደረገለትና በዚህም ተማሪዎች በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ትምህርታቸውን ለመከታተል ተገደው መቆየታቸውን አስታውሰው የተከናወነው የማሻሻያ ግንባታ ከደረጃ በታች የነበረውን ትምህርት ቤት ደረጃው እንዲሻሻል እንደሚግዝ ገልጸዋል።

የማሻሻያ ግንባታው ከመማሪያ ክፍሎች በተጨማሪ ሦስት የአስተዳደር ክፍሎችና በአንድ ጊዜ 14 ተማሪዎችን የሚያስተናግድ የውሃ ቧንቧዎችን ማካተቱን  ተናግረዋል፡፡

የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ ነጋ አብርሀም በበኩላቸው አሸባሪው የህወሓት ቡድን በበርካታ የትምህርት ተቋማት ላይ ከፍተኛ ዝርፊያና ውድመት አድርሷል ብለዋል።

የትምህርት ተቋማቱ መውደም የትምህርት ጥራትንና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ላይ ጫና ማሳደሩን ጠቅሰው፣ ከዚህ ችግር ለመውጣት የጋራ ርብርብ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

ትምህርት ቤቶችን መልሶ ሥራ ለማስጀመርና ከትምህርት ገበታ ውጭ የሆኑ ተማሪዎችን ለመመለስ በውጪ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ድጋፍ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

አሜሪካ  የሚኖሩት ዶክተር አሰረሱና ቤተሰቦቻቸው ትውልድ መቅረጫና ማነጫ ለሆነው ማክሰኝት አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ላደረጉት ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የጠቅላይ ሚነስትር ዶክተር አብይ አህመድን ጥሪ ተቀብለው ወደ ሀገር ቤት የሚመጡ ሌሎች በውጭ የሚኖሩ ዲያስፖራዎችም የእርሳቸውን አርአያነት እንዲከተሉም ጠይቀዋል።

“የመማሪያ ክፍሎች በየጊዜው ስለማይጠገኑ ለዝናብ፣ ለፀሐይ፣ ለአቧራና ለብርድ ተጋልጠን ትምህርታችንን ለመከታታል ተገደን ቆይተናል” ያለችው ደግሞ ተማሪ  ሒሩት አስማረ ነች፡፡ አሁን ተሻሻሎ በመሰራቱ ምቹ ሁኔታ እንደተፈጠረላቸው ገልጻለች።

ተማሪ ማሪቱ ፀሐይ በበኩሏ፤ በእረፍት ወቅት ንጹህ የመጠጥ ውሃ ለማግኘት ወረፋ ስትጠብቅ የመማሪያ ክፍለ ጊዜዋ ይባክን እንደነበር አስታውሳልች።

በአሁኑ ወቅት በአንድ ጊዜ ብዙ ሰው ማስተናገድ የሚችል ቧንቧ በመገንባቱ ችግራቸው  መቃለሉን ተናግራለች፡፡