በአሸባሪው ህወሃት የተፈጸሙ ወንጀሎችን የሚያጣሩ ቡድኖች ወደ አማራና አፋር ክልሎች ተሰማሩ

52

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 16 ቀን 2014 (ኢዜአ)  በአሸባሪው ህወሃት ተወረው በነበሩ አካባቢዎች ላይ የተፈጸሙ ወንጆሎችን አጣርቶ ወንጀለኞችን ለህግ ለማቅረብ ምርመራ የሚያደርጉ ቡድኖች ወደ አማራና አፋር ክልሎች መላካቸውን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ።

በወራሪ ቡድኑ ተይዘው የነበሩ አካባቢዎች ነጻ በመውጣታቸው ዜጎችን ወደ ቀያቸው ለመመለስ እየተሰራ መሆኑም ተገልጿል።

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መግለጫ ሰጥተዋል።

ሚኒስትር ዴኤታዋ እንዳሉት፤ በአሸባሪው ህወሃት ወረራ ውስጥ በነበሩ አካባቢዎች የተፈጸሙ ወንጀሎችን አይነትና መጠናቸውን በዝርዝር የመለየት ስራ ተጀምሯል።

ለዚህም ይረዳ ዘንድ አሸባሪ ቡድኑ ያደረሳቸውን ሰብአዊና ቁሳዊ ጉዳቶች የሚያጠና የወንጀል ምርመራና የማስቀጣት ቡድን ወደ አማራና አፋር ክልሎች መላክ መጀመሩን ገልጸዋል።  

ከባለፈው ሰኔ ወር ጀምሮ በወራሪው የህወሃት ቡድን የተፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች የተፈጸሙበትን ቦታና መጠን በተመለከተ ተጨባጭ መረጃና ማስረጃ ለመሰብሰብ የመስክ ቅኝቶች የሚደረጉ ይሆናል ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት በአፋር ክልል አንድ መርማሪ ቡድንና ሁለት ንዑሳን ቡድኖች የምርምራ ስራቸውን መጀመራቸውን አመልክተዋል።

በአማራ ክልልም በርከት ያሉ ቡድኖች ተሰማርተዋል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ ሸዋሮቢትን ጨምሮ በሰሜን ሸዋ ዞን አስር ወረዳዎች፣ በደቡብ ወሎ ዞን ስምንት ወረዳዎች፣ በኦሮሞ ብሄረሰብ ልዩ ዞን፣ በደሴና በኮምቦልቻ እንዲሁም ጋሸናን ጨምሮ በሰሜን ወሎ ስር ባሉ ወረዳዎች የምርመራ ስራ መጀመሩን አብራርተዋል።

የምርመራ ቡድኖቹ  በወልደያና በዋግህምራ ተሰማርው ስራቸውን እየሰሩ መሆኑንም ገልጸዋል። 

መርማሪ ቡድኖቹ ምርመራውን የሚያካሂዱት ዓለም አቀፍ መስፈርቶችን ባሟላ መልኩ መሆኑን የተናገሩት ሚኒስትር ዴኤታዋ  ይህም አሸባሪው ህወሃት የፈጸማቸውን ወንጀሎች ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለማስረዳት ያለው ፋይዳ የጎላ መሆኑን አስምረውበታል።   

ከምርመራ ስራው ጎን ለጎን የመልሶ ማቋቋም ስራዎች እየተሰሩ መሆኑንም ሚኒስትር ዴኤታዋ ጠቁመዋል።

አሸባሪው ቡድን በወረራ ይዟቸው ከነበሩት የሁለቱ ክልሎች የተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው በተለያዩ መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ የሚገኙ ዜጎች ድጋፍ እየተደረገላቸው እንደሚገኙ ተናግረዋል።   

በአሸባሪ ቡድኑ የወደሙ ጤና ተቋማት  አስፈላጊው ግብአት ተሟልቶላቸው በፍጥነት ወደ ሥራ እንዲገቡ ሁኔታዎች መመቻቸታቸውንም በመግለጫቸው አብራርተዋል።  

ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ገበታቸው መመለስን ጨምሮ የተለያዩ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን ወደ መደበኛው ስራቸው ማስገባት እንዲቻል የህብረተሰቡ እገዛ እንዲጠናከርም ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም