የህወሓት አሸባሪ ቡድን በጤና እና በትምህርት ተቋማት ላይ ያደረሰው ውድመት የዜጎችን ሠብዓዊ መብት የነጠቀ ነው

86

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 16 ቀን 2014 (ኢዜአ)  አሸባሪው የህወሓት ወራሪ በትምህርትና በጤና ተቋማት ላይ ያደረሰው ውድመት የዜጎችን ሠብዓዊ መብት ከመንጠቁ ባሻገር የቆመለት ዓላማ እንደሌለው ማሳያ ነው ሲሉ የሠብዓዊ መብት ተሟጋቹ ኦባንግ ሜቶ ገለጹ።

ኦባንግ ሜቶ ኢትዮጵያዊያን የሽብር ቡድኑ ያደረሰውን ውድመት መልሶ ለመገንባት በአንድነት እንዲነሱም ጠይቀዋል።

የሠብዓዊ መብት ተሟጋቹ ኦባንግ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ አሸባሪው ህወሓት በሰው ሕይወትና ንብረት ላይ ያደረሰውን ኢ-ሠብዓዊ ድርጊት ኮንነዋል።

ወረራ በፈጸመባቸው የአገሪቷ አካባቢዎች ሰዎችን በግፍ መግደሉ ሳያንስ የሕክምና ተቋማት ላይ ትኩረት አድርጎ ማውደሙ ሠብዓዊነት የጎደለው መሆኑን ያሳያል ብለዋል።

በጦርነት ወቅት የማይነኩ ነገሮች አሉ ያሉት ኦባንግ በጥላቻ የታወረው የህወሓት የሽብር ቡድን ዜጎችን በመግደል ከሞት የተረፉትም እንዳይታከሙ ጤና ተቋማትን ማውደሙን ተናግረዋል።

የሽብር ቡድኑ ወረራ በፈጸመባቸው የአማራና የአፋር ክልሎች የእውቀት መቅሰሚያ የሆኑ ትምህርት ቤቶችን ወደ ፍርስራሽነትና ጅምላ መቃብርነት መቀየሩንም እንዲሁ።

ለዜጎች ሠብዓዊ መብቶች የሆኑትን አገልግሎት የሚሰጡ የጤና እና የትምህርት ተቋማትን ማውደሙ የሽብር ቡድኑ ዓላማ እንዳሌለው የሚሳይ መሆኑን ነው የገለጹት።

ቡድኑ ኢትዮጵያን ለማፍረስ የያዘውን ዕቅድ የነገ አገር ተረካቢዎች መፍለቂያ የሆኑ የትምህርት ተቋማትን በማውደም ጭምር ማሳየቱንም የሠብዓዊ መብት ተሟጋቹ ተናግረዋል።

ቡድኑ ውስጡን በቂም በቀልና በጥላቻ ብቻ ሞልቶ ማንነቱን በመርሳት የሰዎችን በሕይወት የመኖር፣ የመንቀሳቀስ፣ አገልግሎት የማግኘትና ሌሎች ሠብዓዊ መብቶችን መግፈፉንም አክለዋል።

በመሆኑም ኢትዮጵያዊያን በአገራቸው ሕልውና የመጣውን ጠላት ለመደምሰስ ያሳዩትን አንድነትና ትብብር ተፈናቃዮችን በሟቋቋምና የወደሙ ተቋማትን ወደ አገልግሎት ለመመለስ እንዲደግሙት ጥሪ አቅርበዋል።

በጦርነቱ የተሰቃዩ፣ የተደፈሩና ቤተሰቦቻቸውም ላይ የሚደርሰውን የስነ-ልቦና ቀውስ ለማከምም ሙያተኞች መተባበር እንዳለባቸው አመልክተዋል።

ኦባንግ ሜቶ የሽብር ቡድኑ ለማንም ርህራሄ የሌለውና የቆመለት ዓላማ ካለመኖሩ አንጻር በአፋርና በአማራ ክልሎች የፈጸመውን ጭካኔ በትግራይ ክልልም ከመፈጸም ወደኋላ እንደማይል ስጋታቸውን ገልጸዋል።

አሸባሪው የህወሓት ቡድን ወረራ በፈጸመባቸው አማራና አፋር ክልሎች ንጹሃንን በመግደል፣ የዜጎች መገልገያ መሰረተ ልማቶች ሲያወድምና ሲዘርፍ መቆየቱ ይታወቃል።

አሸባሪው የህወሓት ቡድን በፈጸማቸው ግድያ፣ ዘረፋና ውድመት ወንጀሎች በሕግ ሊጠየቅ ይገባልም ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም