ኢንስቲትዩቱ የጂኦስፓሻል መረጃ ለሚፈልጉ ተቋማት ተደራሽ እያደረገ ነው

73

ታህሳስ 16 ቀን 2014 (ኢዜአ) የጂኦስፓሻል መረጃዎችን ለሚሹ ተቋማት ተደራሽ እያደረገ መሆኑን የጂኦስፓሻል ኢንፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ገለጸ።

ኢንስቲትዩቱ ለመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎችና የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ሰጥቷል።

በመርሃ-ግብሩ ኢንስቲትዩቱ ላለፉት 70 ዓመታት የጂኦስፓሻል መረጃዎችን በማዘጋጀት በአገሪቷ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት የራሱን አሻራ ማሳረፉ ተመላክቷል።

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቱሉ በሻ፤ ተቋሙ የጂኦስፓሻል መረጃዎችን በማቀበል ረገድ ለአገር እድገት መሰረት መሆኑን ተናግረዋል።

ጂኦስፓሻል ለገጠርና ለከተማ ልማት፣ ለመንገድ ሥራና ተመሳሳይ መሰረተ ልማቶች ቅድመ ጥናት ላይ የጎላ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።

ከመሬት አስተዳደርም ጋር በተገናኘ ጉልህ ጠቀሜታ እንዳለውም ነው የገለጹት።

ኢንስቲትዩቱ ላለፉት አሥርት ዓመታት ከመሰረተ ልማቶች ግንባታ ጋር ተያይዞ ወሳኝ ሥራዎችን መስራቱንም ተናግረዋል።

ኢንስቲትዩቱ የመሬት አስተዳደርን ከማዘመን ጋር በተያያዘ የመሬት ምዝገባ ፕሮግራሞችን ተግባራዊ እያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።

ይህንንም መደገፍ የሚያስችሉ የአየር ፎቶግራፎችን ለሚፈልጉ ተቋማት መረጃዎችን ተደራሽ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በኢንስቲትዩቱ የጂኦስፓሻል ኢኖቬሽንና አናሊቲክስ ማዕከል ኃላፊ ሙሉዓለም የሺጥላ በበኩላቸው፤ የጂኦስፓሻል መረጃ መሬት ላይ ሊወርዱ የሚችሉ ፖሊሲዎችን ለማውጣት ያግዛል ብለዋል።

ነባራዊ ሁኔታን ያገናዘቡ ሥራዎች መሥራት የሚያስችል ቁልፍ መረጃ እንደሆነም ነው የገለጹት።

አገሪቷን ከመሬት ከሚገኝ ኃብት ተጠቃሚ ማድረግ የሚያስችል መረጃ እንደሆነም አመላክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም