የህወሃት ሽብር ቡድን በህዝብና በተቋማት ላይ የፈጸመው ግፍ ታሪክ ይቅር የማይለው የሚያሳፍር ነው

80

ደሴ፤ ታህሳስ 16/2014 (ኢዜአ) አሸባሪው ህወሓት በህዝብና በተቋማት ላይ የፈጸመው ግፍ ታሪክ ይቅር የማይለው የሚያሳፍር ነው ሲሉ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ተናገሩ።

በአቶ ገዱ  የተመራ ልዑክ በደሴ ከተማ  አሸባሪው ቡድን የደረሰውን ውድመት በተመለከቱበት ወቅት እንዳሉት፤ኢትዮጵያን ለማፍረስ የተነሳው ወራሪው ቡድን በአማራ እና አፋር ክልሎች  ወሮ በያዛቸው አካባቢዎች ያልፈጸመው አስነዋሪ ግፍና በደል የለም፡፡

የህዝብ መገልገያ ሆስፒታሎችን፣ ትምህርት ቤቶችን፣ ሆቴሎችንና የግለሰብ መኖሪያ ቤቶችን ጭምር ከመዝረፍ ባለፈ ዳግም አገልግሎት እንዳይሰጡ አድርጎ ማውደሙ ለህዝቡ ያለውን ጥላቻ ያሳያል ብለዋል።

"የሽብር ቡድኑ በንፁሀን ዜጎችና በንብረት ላይ የፈጸመው ግፍ ታሪክ ይቅር የማይለው የሚያሳፍር ነው" ሲሉም አክለዋል።

"አሸባሪው ህወሓት የፈጸመው ግፍም ለታሪክ ይሰናዳል፤ የልጅ ልጆቻችንም ይማሩበታል" ያሉት አቶ ገዱ፤ የወደሙ ተቋማትና መሰረተ ልማቶችን ሥራ ለማስጀመር በቅንጅት እንደሚሰራ ገልጸዋል።

"የጥፋት ቡድኑ ወረራ በፈጸመባቸው አካባቢዎች የተጎዱ ወገኖች መልሰው እንዲቋቋሙ መንግስት ህብረተሰቡን፣ ተቋማትንና ሌላውንም በማስተባበር ጥረት ያደርጋል" ብለዋል።

አቶ ገዱ፤ የአሸባሪው  ርዝራዦች ለማጥፋት፣  የተጎዱ ተቋማትና መሰረተ ልማቶች ተሰርተው ዳግም ሥራ እንዲጀምሩ ሁሉም የድርሻውን ማገዝ እንደሚጠበቅበትም አመልክተዋል።

የሽብር ቡድኑ ዳግም ስጋት እንዳሆንና የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በዘላቂነት ለማስጠበቅ ወጣቱ መከላከያ ሠራዊትን በመቀላቀል አባቶቹ ያቆዩለትን ሀገር በደሙ ማስቀጠል እንዳለበትም መልዕክት አስተላልፈዋል።

የብልጽግና ፓርቲ ፖለቲካ ዘርፍ ምክትል ኃላፊ አቶ ሙሳ አህመድ በበኩላቸው "አሸባሪው የህወሓት በወረራቸው አካባቢዎች ከፍተኛ ጉዳት ቢያደርስም አንድነትን፣ መተጋገዝንና መተዛዘንን አስተምሮናል" ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ህዝብ የውጭ ጫናውን ለማቃለል አንድነቱን ጠብቆ ለሠራዊቱና ለተፈናቃይ ወገኖች  ያሳየው አጋርነት የሚደነቅና በታሪክ የሚዘከር መሆኑንም ገልፀዋል።

"ህብረተሰቡ ኢትዮጵያዊ የመረዳዳትና የአብሮነት እሴቱን አጉልቶ ይህን አስቸጋሪ ወቅት በጋራ ለማለፍና የወደመውን መልሶ ለማልማት እያሳየ ያለው ቁርጠኝነትን መንግስት ያደንቃል፤ ያበረታታል" ብለዋል።

ተቋማትን መልሰው በመገንባት ለህዝብ አገልግሎት እንዲሰጡ በቅንጅት እንደሚሰሩም አስታውቀዋል።

አሸባሪው ህወሓት የጤና ተቋማትን ጭምር መዝረፉና ያልቻለውን ማውደሙ ሰብዓዊነት የማይሰማው ጨካኝ መሆኑን በተግባር እንደሚያሳይ የገለጹት ደግሞ የደሴ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅ ዶክተር ሃይማኖት አየለ ናቸው፡፡

በሽብር ቡድኑ የጥፋት ተግባር ሆስፒታሉ ሙሉ በሙሉ መውደሙን አውስተው፣ በሆስፒታሉ ላይ ከ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት ውድመትና ዘረፋ መፈጸሙን ጠቅሰዋል።

ሆስፒታሉን መልሶ ወደ ሥራ ለማስገባት  በተደረገው ጥረትም ለድንገተኛና ወላድ እናቶች አገልግሎት መስጠት መጀመሩን ገልጸዋል፡፡

ሆስፒታሉን በሙሉ አቅሙ ሥራ ለማስጀመርም ከመንግስትና ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን አመላክተዋል።

በመረሃ ግብሩ  ላይ የፌዴራልና የደሴ ከተማ አመራሮችና ባለድርሻ አካላት የተሳተፉ ሲሆን በአሽባሪው ቡድን ጉዳት የደረሰባቸው የደሴ ቲሹ ካልቸር፣ ወሎ ዩኒቨርሲቲ ደሴ ካምፓስ፤ ደሴ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታልን፣ ሆቴሎችና ሌሎች ተቋማትን ተዘዋውረው ተመልክተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም