በጉጂ ዞን 19 የሸኔ አባላት እጃቸውን በሰላም ሰጡ

69

ነገሌ፣ ታህሳስ 15 ቀን 2014 (ኢዜአ) በጉጂ ዞን በንጹሀን ላይ ጥቃት ለመፈጸም ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የአሸባሪው ሸኔ 19 አባላት ትናንት እጃቸውን በሰላም መስጠታቸውን የዞኑ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምሪያ ዕዝ ኮሚቴ አስታወቀ፡፡

የኮሚቴው አባል የዞኑ ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ኮማንደር ብዙነህ ቦዲና እንደገለጹት፤ የቡድኑ አባላት  እጃቸውን በሰላም የሰጡት በአዶላ ወዩ ሊበን እና ጎሮዶላ ወረዳዎች ውስጥ ነው፡፡

ከመካከላቸውም  ሶስቱ ከነሙሉ ትጥቃቸው እጅ መስጠታቸውን ጠቁመዋል።

ከዚህም ሌላ በፌደራል፣ በክልሉና በዞኑ የጸጥታ ሀይሎች ባለፉት አራት ቀናት በተካሄደ ኦፕሬሽን እጅ በሰላም ለመስጠት ፈቃደኛ ያልሆኑ 22 የቡድኑ አባላት እንደተደመሰሱም አስታውቀዋል፡፡

በዞኑ በንጹሀን ላይ የሚያደርሰውን ጥቃት ለማስቆም በጸጥታ ሀይሎቹ ጥምረት የሚወሰደው እርምጃ አሁንም ተጠናክሮ ቀጥሏል ብለዋል፡፡

የኮሚቴው ሰብሳቢ የሆኑት የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታደለ ኡዶ በበኩላቸው፤ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ በሽብር ቡድኑ ተታለው ወደ ጫካ የገቡ ሰዎች  እጃቸውን በሰላም ለመስጠት አሁንም አልረፈደም ብለዋል፡፡

የመንግስት የጸጥታ ሀይሎች በሚወስዱት እርምጃ የሽብር ቡድኑ ሰብአዊና ቁሳዊ ኪሰራ እየደረሰበት በመሆኑ ተታለው የነበሩ  ሰዎችም  ለመንግስት እጃቸውን እየሰጡ ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡

እጃቸውን ከሰጡ የአሸባሪው ቡድን አባላት መካከል  ጸጋዬ ቱሉ በሰጠው አስተያየት፤ ተታሎ  ከቡድኑ ጋር የተቀላቀለው ከስድስት ወራት  በፊት እንደነበር ያስታውሳል፡፡

የቡድኑን ዓላማ በመቃወም እሱና ሌሎች አምስት ሰዎች ጠፍተው ለማምለጥ ቢሞክሩም ተይዘውና ታስረው ለጥፋት እንዲሰማሩ ተገደው እንደነበርም ጠቅሷል፡፡

እርስ በርስ እንዳንተማመን በአካባቢና በጎሳ ስለተከፋፈልን የተሰጠንን ተልእኮ ከመፈጸም በስተቀር መጠየቅም ሆነ ቅሬታ ማቅረብም አንችልም ነበር ብሏል፡፡

ከቡድኑ አምልጬ እጄን በሰላም ለመንግስት መስጠት በመቻሌ ተደስቻለሁ፤ የበደልኩትም ህዝብ ይቅርታ እጠይቃለሁ፤ ሌሎች ወጣቶችም ከዚህ ሊማሩ ይገባል ሲል ገልጿል፡፡

ሌላው እጁን በሰላም የሰጠው አልዬ አብዱረህማን በበኩሉ፤ ተታሎ ከቡድኑ ጋር በመቀላቀል ለሁለት ዓመታት አብሮ ለመቆየት መገደዱን ነው የገለጸው።  

ኦሮሞን ነጻ እናውጣ ብለው በስልክ ሲጠሩኝ እውነት መስሎኝ በፍላጎቴ ከተቀላቀልኩ በኋላ እርስ በእርስ መገዳደሉ አይበጅም ብልም ሰሚ አላገኘሁም ብሏል፡፡

በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ሽብርተኛው ሸኔን የተቀላቀሉ ወደ ሰላም እንዲመለሱ፤ በግንዛቤ ጉድለት ቡድኑን ለመቀላቀል ያሰቡ ካሉም ቆም ብለው እንዲያስቡ መልዕክት አስተላልፏል፡፡

የሽብር ቡድኑ እንኳን ኦሮሞን ነጻ ሊያወጣ እራሱም በጎሳና በዓላማ ተከፋፍሎ እየተበተነ እንደሆነ  የተናገረው ደግሞ ሌላው እጁን ለመንግስት በሰላም የሰጠው ቀጀላ ጫላ ነው።

ባለማወቅ የሽብር ቡድኑን በመቀላቀል ለሰራሁት ስህተት ይቅርታ እጠይቃለሁ፤ የበደልኩትን ህዝብም ለመካስ ዝግጁ ነኝ ብሏል፡፡

_ አካባቢህን ጠብቅ፣

_ ወደ ግንባር ዝመት፣

_ መከላከያን ደግፍ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም