አሸባሪው ለሰላም ብሎ እንደወጣ አድርገው አንዳንድ የውጭ ሚዲያዎችን የሚያሰራጩትን የሀሰት ዘገባ ማጋለጥ ይገባል

ባህርዳር ፤ታህሳስ 15/2014 (ኢዜአ) በወገን ሃይል ሽንፈት የተከናነበውን አሸባሪ ቡድን ለሰላም ብሎ ወረራ ከፈጸመባቸው አካባቢዎች እንደወጣ አድርገው አንዳንድ የውጭ ሚዲያዎችን የሚያሰራጩት የሀሰት ዘገባ ማጋለጥ እንደሚገባ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ተናገሩ።

በነገው ዕለት  በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ በጋራ ያዘጋጁት የውይይት መድረክ ይካሄዳል።

አምባሳደሩ  በወቅታዊ ጉዳይና በነገው ውይይት ዙሪያ  ዛሬ በሰጡት  መግለጫ ኢትዮጵያ እያካሄደች ያለችውን የህልውና ዘመቻ በማገባደድ ላይ ትገኛለች ብለዋል።

ጦርነቱ አብቅቷል ከማን ጋር ነው የምንደራደረው "ሲል የነበረው አሸባሪው የህወሃት ቡድን በወገን ሃይል በደረሰበት ተከታታይ ምት የተሸነፈ መሆኑን አውስተዋል።

ሆኖም አንዳንድ የውጭ ሚዲያዎች አሸባሪው በወረራ ይዟቸው ከነበሩ የአማራና አፋር ክልሎች ተሸንፎ መውጣቱን እያወቁ ለሰላም ሲል እንደወጣ አድርገው መዘገባቸው ስህተት መሆኑን ገልጸዋል።

የህልውና ዘመቻውን ስኬት አጣመው እውነትን በመካድና አሸባሪ ቡድኑን በሚደግፍ መልኩ መዘገባቸው ትክክል አለመሆናቸውን የሀገራችንና  የወዳጅ ሀገራት ሚዲያዎች ሊያጋልጡ ይገባል ብለዋል።

እነዚህ ሚዲያዎች በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ያላቸው እይታ ታሪክን አጣሞ በማቅረብና በውሸት ላይ የተመሰረተ መሆኑን ከዚህ በላይ ማረጋገጫ የለም ነው ያሉት አምባሳደር ዲና።

በነገው ዕለት  በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ በጋራ ያዘጋጁት የውይይት መድረክ ይካሄዳል።

ይህም ምሁራን ያላቸውን እውቀትና ክህሎት ተጠቅመው የምዕራባውያን ሚዲያዎችንና ድርጅቶችን እንዲሞግቱ የሚያስችል እንደሆነ አስረድተዋል።

ሚንስቴሩ የሀገራችን የውጭ ግንኙነት ከሀገር ህልውና ጋር በማስተሳሰር መስራት በመቻሉ አፍሪካውያን ወንድሞቻችንና እህቶቻችንን ከጎናችን ለማሰለፍ አብቅቶናል ብለዋል።

ይህም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት የኢትዮጵያን ጉዳይ ከ10 ጊዜ በላይ አጀንዳ አድርጎ ቢያቀርብም በወንድሞቻችንና በወዳጆቻችን ጥረት ማክሸፍ መቻሉን አንስተዋል።

"ድርጊቱ በህዳሴው ግድብ ግንባታ ላይም ተደግሟል" ያሉት አምባሳደር ዲና፤ ጠላቶቻችን አሁንም በህልውና ዘመቻው ላይ ከአሸባሪው ቡድን ጎን በመሰለፍ ከኢትዮጵያ ጀርባ ላይ አልወረዱም ሲሉ ተናግረዋል።

በወገን ምት እየሞተ ያለውን የህወሃት አሸባሪ ቡድን ህልውና እንዳለው አስመስለው የሚያቀርቡበት ሁኔታ ሲታይ በሞተ ነገር ላይ ነፍስ የመዝራት ያህል በመሆኑ እስከመጨረሻው መመከት እንደሚገባ ተናግረዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ መሰረት ወደ ሀገር ቤት እንደሚመጡ የሚጠበቁት ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያንና የሌሎች ሀገራት ዜጎች ወደ ሀገራችን መምጣት የጀመሩበት ወቅት መሆኑን አብራርተዋል።

የእነዚህ ወገኖች መምጣትም አሁን በተፈጠረው ሁኔታ ከወገናቸው ጎን ለመሰለፍ፣ በሀገራችን ላይ የተፈጠረውን ጫና ለመመከትና በመልሶ ግንባታው የድርሻቸውን እንዲወጡ የሚያግዝ  ነው ብለዋል።

ዲያስፖራው በመልሶ ግንባታው ላይ ንግድና ኢንቨስትመንት በማንቀሳቀስ፣ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችንና አሰራሮችን በማምጣትና የሃብት ምንጭ በመሆን ሀገራቸውን የሚጠቅሙበት እድል እንደሚፈጥር ተገልጿል።

በጦርነቱ ተቀዛቅዞ የነበረውን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴ ለማንሰራራት የሚያስችል መሆኑን በመግለጫው ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም