የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ወቅታዊ መረጃ ከማድረሱ በተጓዳኝ በመልሶ ማቋቋም ሂደት የድርሻውን ይወጣል

252

ደሴ ፤ ታህሳስ 15/2014 (ኢዜአ)የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ለህብረተሰቡ ወቅታዊ መረጃ ከማድረሱ በተጓዳኝ በአሻባሪው ቡድን ጉዳት የደረሰባቸውን መልሶ ለማቋቋም የድርሻውን እንደሚወጣ የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጌትነት ታደሰ ገለጹ፡፡

ድርጅቱ ለደቡብ ወሎ ዞንና ደሴ ከተማ አስተዳደሮች፣ ለአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽንና ለተፈናቃይ ወገኖች  ከ5 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የቢሮ መገልገያዎችና ምግብ ነክ ድጋፍ ዛሬ አድርጓል፡፡

ዋና ሥራ አስፈጻሚው ድጋፉን በደሴ ከተማ ተገኝተው ባስረከቡበት ወቅት እንዳሉት፤ ድርጅቱ አሸባሪው የህወሓት ቡድን ያደረሰውን ውድመት መልሶ ለማቋቋም የድርሻውን ይወጣል።

በዚህም ለተቋማቱ የቢሮ መገልገያ ጠረጴዛዎችና ወንበሮች ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል።

እንዲሁም  ለተፈናቃዮች 25 ኩንታል ዱቄት፣25 ኩንታል ማካሮኒ፣ 25 ኩንታል ፓስታ እንዲሁም  አልባሳት ለግሰዋል፡፡

ድርጅቱ በተለይ ለአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን(አሚኮ) የቢሮ መገልገያዎች ድጋፍ  ያደረገው በአሸባሪው ህወሓት ውድመት የደረሰበትን ን የደሴ ቅርንጫፍ መልሶ ለማቋቋም እንዲያግዝ መሆኑን ተናግረዋል።

አሸባሪው ቡድን በአማራና አፋር ክልሎች ያደረሰው ውድመት ለህዝብ ያለውን ጥላቻና የአስተሳሰብ ውድቀት ያሳያል ያሉት  አቶ ጌትነት፤መገናኛ ብዙሃን በመልሶ ማቋቋም ሂደት ድጋፍ በማድረግ  ህዝባዊነታቸውን ማሳየት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡

የደቡብ ወሎ ዞን አስተዳዳሪ አቶ አብዱ ሁሴን ፤ድርጅቱ ላደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

ተቋማት፣ዳያስፖራውና ህብረተሰቡ በአሸባሪው ቡድን የተጎዱትን ወገኖችና ተቋማት መልሶ ለማቋቋም የተጀመረውን እንቅስቃሴ እንዲያጠናክሩ ጠይቀዋል፡፡

በዞኑ በአሸባሪው ህወሓት የወደሙ ተቋማትን በመጠገንና መልሶ ሥራ ለማስጀመር ኮሚቴ ተቋቁሞ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ደረጀ ሞገስ በበኩላቸው፤ ድርጅቱ  ወቅታዊና ትክክለኛ መረጃ ለህዝብ በማድረስ የህዝብ ድምጽ በመሆኑ በአሸባሪው ቡድን ጥቃት እንደተፈጸመበት ገልጸዋል፡፡

በደሴ ቅርንጫፍ የነበረውን ንብረት ዘርፎ፤ ያልቻለውን ደግሞ አገልግሎት እንዳይሰጥ ሙሉ በሙሉ አውድሞታል ብለዋል፡፡

ድርጅቱ ካለው በማካፈል አጋርነቱንና ለጋራ ዓላማ መቆሙን በተግባር በማሳየቱ ምስጋና አቅርበዋል፡፡