ሕብረተሰቡ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል የሚያደርጋቸው ጥንቃቄዎች ላይ መዘናጋቶች እየተስተዋሉ ነው

96

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 15 ቀን 2014 (ኢዜአ) ሕብረተሰቡ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል የሚያደርጋቸው ጥንቃቄዎች ላይ መዘናጋቶች እየተስተዋሉ መሆኑን ኢዜአ ያነጋገራቸው የጤና ባለሙያዎች ተናገሩ።

ሕብረተሰቡ የወረርሽኙን መከላከያ መንገዶች አጠብቆ መተግበር አለበት ብለዋል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ278 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በኮቪድ-19 ወረርሽኝ መያዛቸውንና ከ5 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ ሰዎችም በወረርሽኝ ምክንያት ሕይወታቸውን እንዳጡ ከአሜሪካ የጆን ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ የመረጃ ቋት የተገኘው መረጃ ያሳያል።

እስከ ትናንት ድረስ በኢትዮጵያ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ በአጠቃላይ 386 ሺህ 164 የተያዙ ሲሆን፤በቫይረሱ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 6 ሺህ 885 መድረሱን የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።

በትናንትናው ዕለት ብቻ በቫይረሱ 3 ሺህ 793 ሰዎች ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል።

በኢትዮጵያ ከሁለት ሳምንት ወዲህ የኮቪድ-19 ምጣኔ በተከታታይ የጨመረ ሲሆን፤ ከነበረበት 3 በመቶ ወደ 28 በመቶ ከፍ ብሎ መገኘቱን ጤና ሚኒስቴር ገልጿል።

የኢትዮጵያ ሕክምና ማህበር ምክትል ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር አመዘነ ታደሰ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የኮሮና ቫይረሰ ወደ ኢትዮጵያ በገባበት ጊዜ ተገቢው ጥንቃቄ ሲደረግ ቢቆይም አሁን መዘናጋቶች እየተስተዋሉ ነው።

ይህን ተከትሎ ኅብረተሰቡ ለወረርሽኙ ተጋላጭ እንዳይሆን የጥንቃቄ እርምጃዎችን ማጠናከር እንዳለበት ገልጸዋል።

በመሆኑም ሕብረተሰቡ መዘናጋት ዋጋ እንዳያስከፍለው ቫይረሱን ለመከላከል ሲተገብራቸው የነበሩ የጥንቃቄ ተግባራትን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል።

ማህበሩ የጤና ባለሙያዎችና ኅብረተሰቡ ስለ ቫይረሱ ያላቸውን ግንዛቤ ለማሳደግ የግንዛቤ መፍጠሪያ ሥራዎችን ሲሰራ መቆየቱንና ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል።

በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ግብረ ሃይል አስተባባሪ ዶክተር ደሳለኝ ቀነኒ በሽታው የቀነሰ መስሎ በአጭር ጊዜ እያገረሸና በማዕበል መልክ አይነቱን ቀይሮ እየተከሰተ መሆኑን ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ አራተኛው የወረርሽኙ ማዕበል መከሰቱን ተከትሎ በኢትዮጵያም የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ ኅብረተሰቡ የመከላከያ ተግባራትን አጠናክሮ ሊተገብር ይገባል ብለዋል።

ኅብረተሰቡ ርቀቱን በመጠበቅ፣ የአፍና አፍንጫ ጭንብል በማድረግ እንዲሁም የእጅ ንፅህናን መጠበቅ እንዳለበት ገልጸዋል።

መሰባሰብ ግድ በሚልባቸው በትምህርት ቤቶች፣ በአምልኮ እና በገበያ ስፍራዎች ጥንቃቄው መዘንጋት እንደሌለበት አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም