ኢትዮጵያ በምትፈልገው ሁሉ አለንልሽ በማለት ጥሪውን ተቀብለን መጥተናል

68

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 15 ቀን 2014 (ኢዜአ)  ኢትዮጵያ በምትፈልገው ሁሉ አለንልሽ በማለት መጥተናል ሲሉ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድን ጥሪ ተቀብለው ከአሜሪካ የተለያዩ ግዛቶች የመጡ ዳያስፖራዎች ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ለገና በዓል አንድ ሚሊዮን ኢትዮጵያዊያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያዊያንና የኢትዮጵያዊያን ወዳጆች ወደ አገር ቤት እንዲገቡ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል።

ይህንንም ተከትሎ በርካታ ቁጥር ያላቸው ዳያስፖራዎች ወደ አገር ቤት እየገቡ ነው።

ኢዜአ ዛሬ በቦሌ ዓለም አቀፍ የመንገደኞች ተርሚናል በመገኘት ጥሪውን ተከትሎ ወደ አገር የገቡትን ዳያስፖራዎች አነጋግሯል።

በአሜሪካ ቺካጎ የሚኖረው አቶ አማኑኤል አሰፋ ምዕራባውያን በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርሱትን ጫና በመቃወም ‘በቃችሁ ብለን” ወደ አገር ቤት መጥናል ብለዋል።

በሕጋዊ መንገድ ገንዘብ በመመንዘር የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ እንደሚደግፉ ተናግረዋል።

በአሜሪካ ሚዙዩሪ ግዛት የሚኖሩት አቶ ኤርሚያስ አያሌው በበኩላቸው ኢትዮጵያ የጠየቀችኝ ነገር ለማድረግ ዝግጁ ነኝ፤ ሌላውም ዳያስፖራ በጥሪው መሰረት አስፈላጊውን ድጋፍ ሊያደርግ ይገባል ብለዋል።

ምዕራባውያን መገናኛ ብዙሃን ኢትዮጵያ ሰላም አይደለችም ተረብሻለች እያሉ የሐሰት ዘገባ ቢያወጡም እኛ አገራችን ሰላም መሆኗን አይተናል ያሉት ደግሞ በዳላስ ቴክሳስ የሚኖሩት ወይዘሮ እልፍነሽ ማሩ ናቸው።

በዳላስ የሚኖሩ የኢትዮጵያ ዳያስስፖራ ማህበረሰብ አባላት ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ እያደረጉ እንደሚገኝና ይሄንንም አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

እንደ ወይዘሮ እልፍነሽ በዳላስ ቴክሳስ የሚኖሩት አቶ ሃብቴ ረታ ''ኢትዮጵያዊ ዜጋ ለአገሩ ክብር በግንባር ሲዋደቅ እኛ ደግሞ አገር ስትጠራን ቲኬት ቆርጦ መምጣት ምንም ማለት አይደለም'' በማለት አገራዊ ጥሪውን ተቀብለው መምጣታቸውን ገልጸዋል።

በአሜሪካ ሚኒሶታ ግዛት የሚኖሩት ወይዘሮ አሰገደች ደስያለው ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸው ቃላት የማይገልጸው ደስታ እንደፈጠረባቸውና የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዳግም እንዲያንሰራራ ዳያስፖራው የሚቻለውን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል ።

በውጭ አገራት የሚኖሩት ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያዊያኑ ስለ አገራቸው በቅርበት ሲከታተሉ እንደነበር በመግለጽ፣ አሁን ደግሞ አገሪቷ በምትፈልገው ሁሉ ለማገዝ በአካል እንደተገኙ አንስተዋል።

በውጭ አገራት የሚኖሩት ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያኑ ምዕራባዊያኑ ኃያላን አገራት በውስጥ ጉዳይ በመግባት በአገር ላይ እያደረጉ ያለውን ጫና አደባባይ ወጥቶ የ’በቃ’ ወይም ‘#NoMore’ ንቅናቄን ሲያደርጉ መቆየታቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም