አፍሪካውያን የዳግም ቅኝ ግዛት እሳቤን ለመቃወምና በራሳቸው ጉዳይ በራሳቸው መወሰን እንዲችሉ አዲስ የትግል ምዕራፍ መክፈት አለባቸው

99

ሀዋሳ ፤ታህሳስ 15/2014 (ኢዜአ) አፍሪካውያን የዳግም ቅኝ ግዛት እሳቤን የሚቃወም አዲስ የትግል ምዕራፍ መክፈት እንዳለባቸው ኢዜአ ያነጋገራቸው የሃዋሳ ዩንቨርሲቲ ምሁራን ገለጹ።

የፓን አፍሪካኒዝም እሳቤን በአፍሪካ አሁን ካለው ተጨባጭ ሁኔታዎች ጋር ማዛመድ እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።

አፍሪካ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በተለይም በፀጥታው ምክር ቤት በቂ ውክልናና ድምፅ እንዲኖራት በየጊዜው ጥያቄዎች የሚያቀርቡ ቢሆንም፤በድርጅቱ ባለው ቢሮክራሲያዊ ውጣ ውረድና ሃያላኑ ተጽዕኖ ምላሽ ሳያገኝ ቀርቷል።

የሃዋሳ ዩንቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አለም አቀፍ ጥናት መምህር ረዳት ፕሮፌሰር አወል አሊ እንዳሉት “የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አሜሪካንን ጨምሮ በአንዳንድ ምዕራባዊያን ሀገራት ቁጥጥር ሥር በመዋሉ የአፍሪካን ጉዳዮች በቸልታ እንዲመለከቱ አድርጓል።”


አመለካከታቸውን ከእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ ያልተላቀቀ በመሆኑም አፍሪካዊያን ይህንን የሚመክቱበት አቅም ሊያደራጁ ይገባል ብለዋል።

የአፍሪካ ሀገራት በራሳቸው አቅም ለማደግና ሰላማቸውን ለማስከበር ሲነሱ ሃያላኑ በተለይም አሜሪካ የተሳሳተ መረጃ በመንዛትና ድርጅቱን እየተጠቀሙበት እንደሆነ እንደሚስተዋልም አመልክተዋል።


አፍሪካዊያን ድርጅቱ በኢትዮጵያ ላይ በሚያደርገው ያልተገባ ፍረጃን ለማስቆም የ"በቃ" ዘመቻ ንቅናቄን በመቀላቀልም ሊደግፉ እንደሚገባም ጠቁመዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የፓን አፍሪካኒዝም እሳቤን በማራመዳቸው አድናቆታቸውን የገለጹት ምሁሩ፤ ሌሎች የአፍሪካ መሪዎች ፈለጋቸውን በመከተል የምዕራባዊያንን የዳግም ቅኝ ግዛት ዕሳቤን የሚቃወም አዲስ ምዕራፍ መክፈት ይገባቸዋል ብለዋል።


አፍሪካውያን የምዕራባዊያን ስውር ፍላጎት ማስፈጸሚያ እንዳይሆኑ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ድምጽ ኖሯቸው መብታቸውን ለማስከበር ተደራጅተው መሰራት እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል።


የሃዋሳ ዩንቨርሲቲ የዓለም አቀፍ ህግ ምሁር ረዳት ፕሮፌሰር አንበሴ ፉራ በበኩላቸው፤ ድርጅቱ በሚያከናውናቸው ተግባራት የአፍሪካ ሀገራትን በእኩልነት የማስተናገድ አቅምም ሆነ ፍላጎት እንደሌለው ከማሳየቱም ባለፈ የቅኝ ገዢዎች ፖሊሲ ማስፈጸሚያ በመሆኑ ተቀባይነቱ ጥያቄ ውስጥ መግባቱን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በገጠማት አሁናዊ ችግር ድርጅቱ የምዕራባዊያን ፍላጎት ለማሳካት ካልሆነ በስተቀር እውነትን የሚሰማ ጆሮ እንደሌለው በሚያሳልፋቸው የተሳሳቱ ውሳኔዎች አረጋግጧል ብለዋል።


አፍሪካዊያን በራሳቸው ጉዳይ በራሳቸው መወሰን እንዲችሉ የአፍሪካ ሕብረትን በማጠናከር በጋራ የሚታገሉበት ወሳኝ ምዕራፍ ላይ እንደሚገኙ ነው ያመለከቱት ምሁሩ።

ለዚህ እውን መሆን ደግሞ ፓን የአፍሪካኒዝምን እሳቤን በማጎልበት እንደ ኢትዮጵያ ያሉ በሉዓላዊነት የማይደራደሩ ታሪክ ያላቸው ሀገራት ጎን ለመሆን መታገልን የማሸነፊያ ዋነኛ ስልትና አማራጫቸው እንዲያደርጉ ጠቁመዋል።

አፍሪካውያን በድርጅቱ ድምጻቸውን የሚሰማበት ዓለም አቀፍ ተቋም እንዲሆን ትኩረት መስጠት አለባቸው ነው ያሉት ዶክተር አንበሴ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም