ባለሃብቶች የአፋር ተፈናቃይ ወገኖችን ሕይወት በዘላቂነት በሚቀይር ኢንቨስትመንት እንዲያተኩሩ ተጠየቀ

69

ሰመራ ታኅሣሥ 15/2014(ኢዜአ)ባለሃብቶች ለአፋር ክልል ተፈናቃዮች ከሚያደርጉት የዕለት ደራሽ እርዳታ ባለፈ ሕይወታቸውን በዘላቂነት በሚቀይር ኢንቨስትመንት እንዲሰማሩ የክልሉ ርዕሰ-መስተዳድር አቶ አወል አርባ ጠየቁ።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን በክልሉ በአሸባሪው ህወሓት ለተፈናቀሉ ወገኖች 16 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው የአይነት ድጋፍ አድርጓል።

ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ  ድጋፉን በተረከቡበት ወቅት እንደተናገሩት ባለሀብቶች በክልሉ አሸባሪው ቡድን በፈጸመው ወረራ ለተፈናቀሉት ወገኖች ያደረጉት ድጋፍ የሚያስመሰግን ነው።

ባለሃብቶች ከእለት ደራሽ እርዳታ ባለፈ በክልሉ በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች በስፋት በመሰማራት የተፈናቃዮችን ኑሮ በዘላቂነት ለመቀየር የበኩላቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

አሸባሪው ህወሀት በክልሉ በፈጸመው ወረራ ከ1 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ለከፋ ችግር መጋለጣቸውን ጠቁመው ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉት ከ300ሺህ በላይ መድረሳቸውን አቶ አወል ጠቅሰዋል።

ተፈናቃዮችን  መደገፍ  ዘርና ድንበር ያልገደበው ሰብዓዊነት መሆኑን አመልክተው፤በተለይ የግል ባለሃብቶች እስከ መልሶ ማቋቋም ባለው እንቅስቃሴ ድጋፍ እንዲያደርጉ አመልክተዋል።

የክልሉ መንግሥት ሙአለ ነዋያቸውን ለሚያፈሱ የአገር ውስጥና የውጭ ባለሃብቶች አስፈላጊውን ድጋፍና ጥበቃ እንደሚያደርግ ርዕሰ መስተዳድሩ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሌሊሴ ነሜ ባለሀብቶች በአሸባሪው ቡድን ወረራ ለክልሉ ተፈናቃዮች 16 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው የአይነት ድጋፍ መላካቸውን ገልጸዋል።
ድጋፉ የምግብ ዘይት፣ማካሮኒና ፓስታ ማካተቱን አስታውቀዋል።

ኮሚሽኑ ከዕለት ደራሽ ዕርዳታ እስከ መልሶ ማቋቋም ባለው ሂደት ተሳትፎ እንደሚያደርግ ኮሚሽነሯ አረጋግጠዋል።

በተጨማሪም በክልሉ የተሻለ ኢኮኖሚያዊ መነቃቃትን ለመፍጠር የሠመራ ኢንዱስትሪ ፓርክን ሥራ ለማስጀመር ጥረት እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።

ኮሚሽኑ የውጭና የአገር ውስጥ ባለሃብቶች ወደ ኢትዮጵያ ለመሳብ ጥረት እያደረገ መሆኑን በመግለጽ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም