የኤች.አይ.ቪ ኤድስ ዳግም የጤና ስጋት እንዳይሆን አመራሩ በቁርጠኝነት ሊሰራ ይገባል—ጤና ሚኒስቴር

192

ድሬዳዋ፣ ታህሳስ 15/2014(ኢዜአ) የኤች.አይ.ቪ ኤድስ ስርጭት ዳግም አገርሽቶ የጤና ችግር እንዳይሆን አመራሩ ከመቼውም ጊዜ በላይ በቁርጠኝነት መስራት እንዳለበት የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ አሳስቡ።

ኤች.አይ.ቪ/ኤድስን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የተሰሩ ተግባራትን የሚገመግም ዓመታዊ ጉባኤ በድሬዳዋ እየተካሄደ ነው።

ለሦስት ቀናት የተዘጋጀውን ጉባኤ ያስጀመሩት የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ድጉማ ባለፉት ሦስት አስርት ዓመታት ከዓለም አቀፍ ለጋሽ ተቋማት ጋር በመሆን ቫይረሱን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ሲሰራ ቆይቷል።

በምርመራ፣ ቫይረሱ ከእናት ወደ ልጅ እንዳይተላለፍ በማድረግ እንዲሁም የፀረ-ኤች አይቪ ሕክምና ተደራሽ በማድረግ በኩል የተከናወኑ ሥራዎች አበረታች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በተለይ ቫይረሱ በደማቸው ካለባቸው ሰዎች 95 በመቶዎቹን ወደ ምርመራ በማምጣት፣ ወደ ምርመራ ከመጡት ደግሞ 95 በመቶዎቹን የፀረ-ኤች.አይ.ቪ ሕክምና በማስጀመር እንዲሁም ሕክምና ከጀመሩት መካከል 95 በመቶዎቹ በደማቸው የሚገኘውን የቫይረስ መጠን ትርጉም አልባ በማድረግ በኩል አበረታች ሥራዎች መሰራታቸውን ጠቅሰዋል።

ይሁንና የተካሄዱ ጥናቶች በኢትዮጵያ ቫይረሱ በደማቸው እንዳለባቸው ከሚገመቱ 622 ሺህ 853 ሰዎች መካከል ወደ ምርመራ መጥተው ራሳቸውን ያወቁት 86 በመቶ መሆናቸውን ዶክተር ደረጀ ገልጸዋል።

የተቀሩት 14 በመቶዎቹ ወደ ምርመራ አለመምጣታቸው በከተሞች በቫይረሱ እንደ አዲስ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ለመምጣቱ ምክንያት መሆኑን አመልክተዋል፡፡

በተለይ በተወሰኑ የአገሪቱ ከተሞችና የተወሰኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ የቫይረሱ ስርጭት መጨመርና በወጣቶች ላይ እንደ አዲስ በደማቸው ወስጥ መገኘት አሳሳቢ ያደረገው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

“ችግሩ አሳሳቢ ቢሆንም አመራሩ በእዚያ ልክ ትኩረት አለመስጠቱ ኤች.አይ.ቪ ዳግም በአዲስ አገርሽቶ ከፍተኛ የጤና ችግር እንዳይሆን የሚል ስጋት ፈጥሯል” ብለዋል፡፡

በመሆኑም አመራሩ ወቅታዊ አገራዊ ችግርን እና የኮቪድ-19 ስርጭትን ከመቋቋም ባለፈ ኤች.አይ.ቪን በፍጥነትና በስልት ለመከላከልና ለመቆጣጠር የተዘጋጀውን የ5 ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ ለመተግበር በቁርጠኝነት እንዲሰራ አሳስበዋል፡፡

“በተለይ እ.ኤ.አ. ከ2019 ጀምሮ የተጀመረውንና በቫይረሱ አዲስ የሚያዙ ሰዎች ላይ የሚደረገውን ክትትልና ቅኝት ውጤታማ ለማድረግ በትጋትና በጥራት በመስራት ኤች.አይ.ቪ የጤና ችግር የማይሆንበት ደረጃ ላይ ማድረስ ይገባል” ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ የማህበረሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጽጌረዳ ክፍሌ በበኩላቸው፣ እ.ኤ.አ. በ2030 ኤች.አይ.ቪ የጤና ችግር በማይሆንበት ደረጃ ላይ ለማድረስ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይ ቫይረሱ በደማቸው ያለባቸውና ለምርመራ ወደጤና ተቋም ያልመጡትን 14 በመቶ የሚሆኑ ሰዎችን ለማግኘት የሚያግዝ ጥናት ተካሂዶ ከዓለም አቀፍ ለጋሽ ተቋማት ጋር ወደ ሥራ መገባቱን አስታውሰዋል፡፡

ሥራው በ620 ጤና ጣቢያዎች ላይ በስፋት መጀመሩን ገልጸው፣ ይህም ቫይረሱ በደማቸው አለባቸው ተብለው ከሚገመቱ ሰዎች መካከል 95 በመቶዎቹን ፈልጎ ለማግኘት እንደሚያስችል ተናግረዋል፡፡

አዲስ በኤች.አይ.ቪ የተያዙ ሰዎችን ለማግኘት የሚደረገው የተናጠል ቅኝትን ለማጠናከር እንደሚያግዝም እንዲሁ።

ዳይሬክተሯ እንዳሉት ጥራት ያለው መረጃ  በመሰብሰብና በመተንተን የሚፈለገውን ሕክምናና ሌሎች ዘርፈ ብዙ ምላሽ በመስጠት ኤች.አይ.ቪ ዳግም የጤና ችግር እንዳይሆን ለማድረግ የአመራሩ ቁርጠኝነት ከመቼውም ጊዜ በላይ ያስፈልጋል።

የድሬዳዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ለምለም በዛብህ የግምገማ መድረኩ በተለይ በቫይረሱ እንደ አዲስ የሚያዙ ሰዎች ላይ በሚደረግ ክትትልና ቅኝት ላይ ጥሩ ተሞክሮዎችን ለመቀመርና ክፍተቶችን በማረም በቀጣይ የተሻለ ስራ ለመስራት እንደሚያስችል ተናግረዋል፡፡

ጉባኤው የፌደራል የተናጠል የኤች.አይ.ቪ ቅኝት አተገባበሮችና ውጤቶች ላይ ግምገማ አካሂዷል።

ከመላው አገሪቱ የተውጣጡ የጤና ባለሙያዎችና የጉባኤ ተሳታፊዎች በድሬዳዋ ጤና ተቋማት ኤች.አይ.ቪን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የተሰሩ አብነታዊ ሥራዎችን ጎብኝተዋል፡፡

ጉባኤው የክልሎች የሥራ አፈጻጸም ግምገማም እያካሄደ ነው።