በኢትዮጵያ ላይ የሚነዙ የተሳሳቱ ትርክቶችን በማረም ገጽታዋን መገንባት ይገባል- አምባሳደር ዲና ሙፍቲ

246

ባህርዳር፣ ታህሳስ 15/2014  (ኢዜአ)  በኢትዮጵያ ላይ የሚነዙ የተሳሳቱ ትርክቶችን በማረም ገጽታዋን ለመገንባት ቅንጅታዊ አሰራር አስፈላጊ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃለ አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ አስታወቁ።

አምባሳደሩ ዛሬ በባህርዳር ከተማ ተገኝተው በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥተዋል።

አምባሳደር ዲና በመግለጫው እንዳሉት ሚኒስቴሩ ከባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር የተሳሳቱ ትርክቶችን ለመቀልበስ የሚያስችል የውይይት መድረክ ነገ ያካሂዳል።

በምክክር መድረኩ በምሁራን ትርክቶችን ለማረም የሚያስችሉ ጽሁፎች ለውይይት ቀርበው የጋራ መግባባት ለመፍጠር አቅጣጫ መያዙን አመልክተዋል።

መድረኩ በዋናነት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከመማር ማስተማር፣ ከምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ባሻገር በዲፕሎማሲ ስራ የበኩላቸውን እንዲወጡ ማስቻል እንደሆነም ጠቅሰዋል።

የሚቀርቡ ጽሁፎችም የምሁራንን እውቀትና ክህሎት በማሳደግ በአገራዊ ተልዕኮው የሚኖራቸውን ሚና ማሳደግ መሆኑን ገልጸዋል።

አሁን ላይ አንዳንድ የምዕራባውያን መገናኛ ብዙሀን ፣ ድርጅቶችና መንግስታት ኢትዮጵያ ላይ የያዙትን የማጠልሸት እንቅስቃሴ በመግታት ገጽታዋን መገንባት የመድረኩ አላማ መሆኑን አመልክተዋል።

አምባሳደሩ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን  ወደ ሀገር ቤት ጥሪን በተመለከተ በመግለጫው አብራርተዋል።