መከላከያ ሰራዊት ነጻ ያወጣቸውን ቦታዎች አጽንቶ እንዲቆይ መወሰኑ ከፍተኛ ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ትርፍ አለው

199

ታህሳስ 15 ቀን 2014 (ኢዜአ) መከላከያ ሰራዊት ነጻ ያወጣቸውን ቦታዎች አጽንቶ እንዲቆይ መወሰኑ የአሸባሪውን ህወሃት ሴራ በማክሸፍ ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ትርፉ ከፍተኛ እነደሆነ ኢዜአ ያነጋገራቸው የቀድሞ ጦር መኮንን እና የታሪክ ባለሙያ ገለጹ።

ውሳኔው የትግራይ ሕዝብ እራሱን ከአሸባሪ ቡድኑ ነጻ ለማውጣት የሚያግዝም  ይሆናል ብለዋል። 

በዘመቻ ለሕብረ ብሔራዊ አንድነት የወገን ሃይል አሸባሪው ቡድን ከአፋር ክልል እና ከምስራቃዊ አማራ አካባቢዎች ነጻ መውጣቱን ተከትሎ ሰራዊቱ የያዛቸውን አካባቢዎች አጽንቶ እንዲቆይ መወሰኑ ይታወቃል።

በቀድሞው የኢትዮጵያ ሰራዊት አገራቸውን ለ34 ዓመታት በጦር መኮንንነት ያገለገሉት እና የኮንጎው ዘማች ጠቅል ብርጌድ አባል የነበሩት ብርጋዴር ጀኔራል ካሳ ወልደሰማዕት የመንግስት ውሳኔ አሳማኝ ነው ይላሉ።

የጠላት ሃይል ተዳክሞ እየተበታተነ ባለበት እና የወገን ሃይል በጥሩ ሞራል ላይ በሚገኝበት ሁኔታ የኢትዮጵያን ጠላት ተከታተሎ እስከመጨረሻው መደምሰስ በጦርነት ይደገፋል ብለዋል።

ነገር ግን  ሰራዊት ጸንቶ እንዲቆይ መንግስት ካቀረባቸው አመክንዮዎች አንጻር ሲታይ በርግጥም ሰራዊቱ ባለበት ተጠናክሮ እንዲቆይ መደረጉ አወንታዊ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።

ለአብነትም አሸባሪው ቡድን የራሱን ሬሳ በመሰብሰብ ጅምላ ግድያ ተፈጽሟል በሚል የኢትዮጵያ መንግስት ላይ ውጫዊ ጫና እንዲፈጠር ለማድረግ ያሰበውን ሴራ ለማክሸፍ ነው የሚለው አሳማኝ አመክንዮ ነው ብለዋል።

በህዝብ ደጀንነት ረገድም የመከላከያ ሰራዊት ወደ ትግራይ ገብቶ ከዚህ በፊት እንደ ደረሰበት ክህደት ከጀርባ ቢወጋ እና ሰራዊቱ እርምጃ ቢወስድ መንግስት ለሽብር ቡድኑና ለጋላቢዎቹ ሴራ ተጋላጭ ይሆናል ብለዋል።

በመሆኑም የመንግስት ወቅታዊ እርምጃ በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ጣልቃ እየገቡ የሚፈተፍቱ የውጭ ሃይላትን አንደበት የሚያዘጋ ነው ባይ ናቸው።

በኢትዮጵያ ጦር ሰራዊት ታሪክ ላይ የሚመራመሩት አቶ ገስጥ ተጫኔ በበኩለቸው መንግስት በራሱ ጥናት ላይ ተመስርቶ ትናንት ይፋ ያደረገው እርምጃ እና ያቀረበው አመክንዮ አሳማኝ እንደሆነ ገልጸዋል።

በተለይም ሰራዊቱ በተቆጣጠረባቸው አካባቢዎች እንዲቆይ መወሰኑ ከፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ አንድምታው አንጻር ትርፉ ከፍተኛ እንደሆነ ገልጸዋል።

አሸባሪው የሕወሃት ቡድን በትግራይ ልጆች ደም ስልጣን ላይ መቆየት እንደሚፈልግ ገልጸው፤ አዲስ አበባ ልንገባ ነው በሚል በግዴታም፤ በውዴታም ወጣቶችን ወደጦር ቢማግድም አከርካሪው ተሰብሮ ተመልሷል።

በዚህም በህዝብ በኩል 'ለምን ተመለሳችሁ፤ ልጆቻቸን የት አሉ' የሚሉ ግፊቶች ሲበረቱበት ከህዝብ ግፊት ለመዳን መንግስትን በመወንጀል ያሰበውን ተንኮል እንደሚፈጽም ገልጸው፤ አሁን ግን ይህ ሴራ አይሳካለትም ብለዋል።

ሰራዊቱ ወደትግራይ ሳይገባ ባለበት ፀንቶ እንዲቆይ መደረጉ አወንታዊ መሆኑን ገልጸው፤ ነገር ግን አሸባሪው ህወሃት ዳግም እንዳያንሰራራ መንግስት እየተከታተለ ሁሉን አቀፍ እርምጃ መውሰድ እንዳለበት መክረዋል።

መንግስት ሰራዊቱ የያዛቸውን አካባቢዎች አጽንቶ እንዲቆይ ማድረጉ አሸባሪው የህወሃት ቡድን ልጆቻችን የትአሉ በሚል ከትግራይ እናቶች ለሚነሳበት ጥያቄ መልስ እንዲሆነውም ጭምር ያሰበውን የክፋት መንገድ የሚዘጋ ውሳኔ መሆኑንም ተናግረዋል።

የመንግስት ውሳኔ በአሸባሪ ቡድኑ የተነሳ ለብዙ ችግሮች የተጋለጠው የትግራይ ህዝብ ከአሸባሪው ህወሃት ፕሮፓጋንዳ በመውጣት እውነቱን ሲረዳ የሽብር ቡድኑን በራሱ ተዋግቶ ነጻነቱን እንዲያውጅም ያደርገዋል ብለዋል።

ከወያኔ በተቃራኒ የቆሙ አገር ወዳድ የትግራይ ተወላጅ ልሂቃንና ፖለቲከኞች ከዝምታ ይልቅ ህዝቡን በማንቃት በኩል ትልቅ የቤት ስራ ሊሰሩ እንደሚገባቸው ጀኔራል ካሳና አቶ ገስጥ ገልጸዋል።

_ አካባቢህን ጠብቅ፣

_ ወደ ግንባር ዝመት፣

_ መከላከያን ደግፍ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም