የወልድያ ዩኒቨርሲቲ ከአሸባሪው ህወሓት ዘረፋ በተረፈው ንብረት እንኳን መስራት እንዳይችል ሆኖ ወድሟል

57

አዲስ አበባ ታህሳስ 15 / 2014 (ኢዜአ) አሸባሪው ህወሓት ወልድያ ዩኒቨርሲቲ ላይ ከፈጸመው ዝርፊያ በተጨማሪ በቀረው ንብረቱ እንኳን ስራ እንዳይጀምር አድርጎ አውድሞታል ሲሉ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የደህንነት አማካሪ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው ገለጹ፡፡

ሚኒስትሩ የሽብር ቡድኑ ከፍተኛ ውድመትና ዝርፊያ ያደረሰበትን የወልድያ ዩኒቨርሲቲን ጎብኝተዋል።

የሽብር ቡድኑ ህወሓት ወራሪ የዘረፈውን የዩኒቨርሲቲውን ንብረት ጭኖ ሲወስድ መውሰድ ያልቻለውን አገልግሎት እንዳይሰጥ አድርጎ አውድሞታል።

ይህን የተመለከቱት ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው የዩኒቨርሲቲው ውድመት የሽብር ቡድኑ አባላት መንግስትን ወይንም ፖለቲከኞችን ሳይሆን ሕዝብን አምርረው የሚጠሉ፤ ሕዝብና የሕዝብ የሆነን ሁሉ ከማጥፋት የማይመለሱ መሆናቸውን ያሳየ ነው ብለዋል።

አሸባሪው ቡድን ወልዲያ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ በደረሰበት ሁሉ የፈጸመው ውድመትና ዝርፊያ ቆሜለታለሁ የሚለው የትግራይ ሕዝብም ሲያፍርበት የሚኖር ጥፋት መሆኑንም ተናግረዋል።

በዚህ ደረጃ በሕዝብ ላይ የከፋ ጥላቻ ከተጠናወተው የሽብር ቡድኑ ተግባር ለቀጣይ ትምህርት መውሰድ ይገባል ያሉት ሚኒስትር ገዱ ዩኒቨርሲቲውም ከቀደመው በተሻለ ሁኔታ መልሶ ይገነባል ብለዋል።

የሰሜን፣ የደቡብ ወሎ እና የኦሮሚያ ልዩ ዞን አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብጹዕ አቡነ ኤርሚያስም ጦርነት በተካሄደባቸው አካባቢዎች ውድመት ይኖራል፤ ነገር ግን በዩኒቨርሲቲው ላይ የደረሰው ተምሬያለሁ ከሚል አካል የማይጠበቅ ነው ብለዋል፡፡

የሽብር ቡድኑ ተግባር ምንም ግብ የሌለው ነው ያሉት ብጹዕነታቸው ይህንን ውድመትና ጥፋት አዲስ አበባ የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች መጥተው በዓይናቸው ቢመለከቱ ሚዛናዊ ፍርድ መስጠት ያስችላል ብለዋል።

"የትግራይ እናት ላከችን" ያለው የጥፋት ሃይል የፈጸመው ድርጊት "እውነት የትግራይ እናቶች ፍላጎት ነው ወይ" ሲሉም ነው የተናገሩት።

ያለፉት ወራት አሸባሪው ህወሓት ካደረሰብን ጉዳት በላይ እስላም ክርስቲያኑ በአንድነት የቆምንበት፣ ለቀጣይም ትምህርት ያገኘንባቸው ነበሩ ያሉት ደግሞ የወልድያ ከተማ የሠላም ኮሚቴ አባል ሃጂ ያሲን እድሪስ ናቸው።

ሃጂ ያሲን የሽብር ቡድኑን ወራሪዎች የፈጸሙት ክፋት፣ ዝርፊያና ውድመት ከሰው ልጅ የማይጠበቅ ነው ብለውታል።

አሸባሪው ህወሓት በወልዲያ ዩኒቨርሲቲ ላይ ከ6 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት ውድመት እንዳደረሰበት ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም