የፌዴራል ሆስፒታሎችን በጦርነቱ ከወደሙ ጤና ተቋማት ጋር በማስተሳሰር ውጤታማ ስራ እየተሰራ ነው

85

ታህሳስ 14/2014/ኢዜአ/ የፌዴራል ሆስፒታሎችንና የአዲስ አበባ ጤና ቢሮን በአሸባሪው ህወሓት ከወደሙ የጤና ተቋማት ጋር በማስተሳሰር መልሶ ለማቋቋምና አገልግሎት ለማስጀመር እየተከናወነ ባለው ሥራ ውጤት እየተመዘገበ መሆኑን ጤና ሚኒስቴር ገለጸ።

የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ የወደሙ የጤና ተቋማትና ቁሳቁስ መልሶ ለማልማት እየተከናወነ ስላለው ተግባር ለጋዜጠኞች ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የፌዴራል ሆስፒታሎችና የአዲስ አበባ ጤና ቢሮን ከወደሙ ሆስፒታሎች ጋር በማስተሳሰር እንዲያለሟቸው ኃላፊነት ተሰጥቷቸዋል።

ይህ የማስተሳሰርና የቅንጅት ሥራ ተቋማቱን ከመገንባት ባለፈ በሰው ኃይልና በቁሳቁስ ማደራጀትንም ያካትታል።

በዚሁ መሰረት ጉዳት ከደረሰባቸው ሆስፒታሎች መካከል 34ቱ በአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ሥር ከሚገኙ ሆስፒታሎችና ከፌዴራል ሆስፒታሎች ጋር መጣመራቸውን ገልጸዋል።

በተጨማሪም 69 የወደሙ ጤና ጣቢያዎች ከክልል ጤና ቢሮዎችና ከግል የጤና ተቋማት ጋር የማጣመር ሥራ ተከናውኗል ብለዋል ዶክተር ሊያ።

በተፈጠረው ትስስር 11 ሆስፒታሎች ድንገተኛና መሰረታዊ አገልግሎት መስጠት የጀመሩ ሲሆን 14ቱ ደግሞ ለአገልግሎት ዝግጁ ሆነዋል ነው ያሉት።

በቀጣይ ሰባት የጤና ተቋማት የሚጀምሩ ሲሆን፤ እስካሁን በአማራና በአፋር ክልሎች 64 ጤና ጣቢያዎች መደበኛና ድንገተኛ አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን አብራርተዋል።

ይህን ተሞክሮ ከዩኒቨርሲቲዎችና ካልተሳሰሩ ክልሎችም ጋር በማስጀመር የጤና ተቋማቱን መልሶ የማቋቋም ሥራው ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

አሸባሪው ህወሓት በንጹሃን ዜጎች ላይ ካደረሰው መጠነ-ሰፊ ችግር በተጨማሪ በመሰረተ ልማቶች ላይ ከፍተኛ ውድመት፣ ዝርፊያና ጉዳት ማድረሱንም አስታውሰዋል።

ከወደሙ መሰረተ ልማቶች መካከል የኅብረተሰቡን የጤና ችግር እየቀረፉ ያሉ የጤና ተቋማትና ቁሳቁስ ተጠቃሽ ናቸው።

በአማራና በአፋር ክልሎች ጤና ተቋማት ላይ ከፍተኛ ውድመት መከሰቱን የጠቀሱት ዶክተር ሊያ፤ በዚህ ሳቢያም ጤና ተቋማቱና ባለሙያዎቹ ከሥራ ገበታ ውጭ ሆነዋል፤ ኅብረተሰቡም ለጤና አገልግሎት እጦት ተዳርጓል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም