የውጭ ግንኙነት የውስጥ ሁኔታ ነጸብራቅ በመሆኑ የውስጡን የሠላም እና የኢኮኖሚ ሁኔታ ማስተካከል ይገባል

238

ታህሳስ 14 ቀን 2014 (ኢዜአ) የውጭ ግንኙነት የውስጥ ሁኔታ ነጸብራቅ በመሆኑ የውስጡን የሠላምና የኢኮኖሚ ሁኔታ ማስተካከል ይገባል ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ተናገሩ።

ሚኒስትር ዴኤታው ይህን ያሉት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በሚዘጋጀው የአዲስ ወግ የውይይት መድረክ ላይ ነው።

አሸባሪው ህወሓት በከፈተው ጦርነት ምክንያት ዲፕሎማሲው በተወሳሰበ ሁኔት ውስጥ እያለፈ እንደሆነ የገለጹት አምባሳደር ሬድዋን፤ አንዳንድ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃንም ድብቅ አጀንዳ በመያዝ ኢትዮጵያ ላይ በተደጋጋሚ ሐሰተኛ ዘገባዎችን እያሰራጩ እንደሚገኙ አንስተዋል።

ይህ ሁነትም ሠብዓዊ ድጋፍ አቅራቢ አካላት ተብለው የሚታወቁትን ተግባርና የጀርባ ፍላጎት በይፋ የተረዳንበት ነውም ሲሉ ተናግረዋል፡፡  

ይሁንና ኢትዮጵያዊያን አንድ በመሆናቸው ከውጭና ከውስጥ ያለውን ግፊት መቋቋም መቻላቸውን ነው የገለጹት።

በኢትዮጵያ ላይ እየተደረገ ያለው ጫና በመላው አፍሪካ የሚደርስና እየደረሰ ያለ ጣልቃ ገብነት በመሆኑ አፍሪካዊያን ለኢትዮጵያ ድጋፋቸውን ማሳየታቸውን አድንቀዋል።

የውጭ ግንኙነት የውስጥ ሁኔታ ነጸብራቅ ነው ያሉት አምባሳደር ሬድዋን የውስጡ የሠላምና የኢኮኖሚ ሁኔታ መስተካከል እንዳለበት ጠቁመዋል።

በውስጥ ጉዳያችን ጠንክረን፣ አንድነታችንን ጠብቀን ከተገኘን ከአገራት ጋር ያለን ግንኙነትም ጠንካራ ይሆናል ብለዋል።

ኢትዮጵያን መግፋት ጉዳት እንደሚያስከትል ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ለዓለም ማሳየታቸውንም ተናግረዋል፡፡

የውይይቱ ተሳታፊዎች ይህንኑ ርዕሰ-ጉዳይ አስመልክተው በሰጡት አስተያየት በሁሉም መልኩ ኢትዮጵያ ላይ በተቃጣው ጦርነት ላይ ድል እንዲገኝ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ድርሻውን ተወጥቷል ብለዋል፡፡

ይህንን በጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ሁነት ለመተካት ጠንካራ ዲፕሎማቶችን ማፍራት እንደሚገባም አመልክተዋል።

የውጭ ሚዲያዎች የየአገራቱን ፍላጎትና የፖለቲካ ሁኔታ ተከትለው ኢትዮጵያ ላይ ዘመቻ መክፈታቸውን ጠቅሰው ይህን ለመመከትም በአገር ውስጥ ተመጣጣኝ የሚዲያ ሥራ መሰራት እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡