ምሁራን ኢትዮጵያ የገጠማትን ፈተና በድል አድራጊነት እንድትወጣ የድርሻቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ

106

ደብረ ማርቆስ፣ ታህሳስ 14 ቀን 2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ ከገጠማት የውስጥና የውጭ ጫና በድል አድራጊነት እንድትወጣ ምሁራን የድርሻቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ።

የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ መምህራንና የአስተዳደር ሠራተኞች የአንዳንድ ምዕራባውያንን ያልተገባ ጫና የተቃወሙበት የ''በቃ'' ዓለም አቀፍ ንቅናቄ ውይይት መድረክ ዛሬ ተካሂዷል።

የዩኒቨርሲቲው ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ይኽይስ አረጉ በውይይት መድረኩ እንደተገሩት፤ አንዳንድ ምዕራባውያን አሸባሪውን ህወሓት በመደገፍ በኢትዮጵያ ላይ ያላቸውን ፍላጎትና ምኞት በግልጽ አሳይተዋል።

 አሸባሪው ቡድን  በሥልጣን ላይ በቆየባቸው ዓመታት ሀገሪቱን አሳልፎ መስጠቱ አሁን ከአንዳንድ ምዕራባውያን እየተደረገለት ላለው ሁለንተናዊ ድጋፍ  ማሳያ እንደሆነ ዶክተር ይኽይስ ጠቅሰዋል።

የአሜሪካና አንዳንድ የአውሮፓ አገሮች እያደረጉት ያለውን ጫናና ጣልቃ ገብነት ለመቀልበስ የ''በቃ'' ዘመቻ ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው አስገንዝበዋል።

ኢትዮጵያ ነጻ ሀገር መሆኗንና የማንም ሃገር ጣልቃ ገብነት እንደማያስፈልጋት በእውቀት ላይ ተመሰርቶ ለዓለም ሕዝብ በማሳወቅ በኩል  ምሁራን የድርሻቸውን እንዲወጡም ጠይቀዋል።

''የምዕራባውያን ተጽዕኖ በኢትዮጵያና  የምሁራን ድርሻ'' በሚል ርዕስ ለመድረኩ ጽሁፍ ያቀረቡት የታሪክ መምህር ዶክተር አዳነ ካሴ አንዳንድ ምዕራባውያን ሀገራት የኢትዮጵያን እምቅ የተፈጥሮ ሀብት የመጠቀም ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል።

ለዚህም የሀገር ተቆርቋሪነትና ሕዝባዊ ወገንተኝነት የሌለውን ዘራፊ ቡድን ስለሚደግፉ የጥቅም አጋራቸውን ውድቀት እንደማይፈልጉ አብራርተዋል።

አሁንም አሸባሪው ህወሃት ቡድን በንጹሀን ላይ ያደረሰውን በደልና ያወደመውን ንብረት ከመጠየቅ  ተቆጥበው ኢትዮጵያን በመኮነን ላይ ተጠምደው ይገኛሉ ብለዋል።

በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ያደረሰውን በደል ዘመኑ ያፈራቸውን ቴክኖሎጂዎች በመጠቀም ለዓለም ህዝብ ማሳወቅ የ''በቃ'' ዘመቻውን እናስቀጥል ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።

በዩኒቨርስቲው የእጽዋት ሳይንስ መምህር ዶክተር ዳሞት አንተነህ ፤ የ''በቃ'' ንቅናቄ በኢትዮጵያ ብሎም በአፍሪካ አዲስ የፖለቲካ እይታ መፍጠሩን ተናግረዋል።

ቀድሞም ለኢትዮጵያ የማይተኙ አንዳንድ የውጭ ሃይሎች በዴሞክራሲና ሰብዓዊ መብት ስም ሊያጠቋት እንደሚፈልጉ በግልፅ አሳይተውናል ብለዋል።

ከውጭ ሃይሎች ተጽዕኖ ለመላቀቅ በራስ አቅም ከኢኮኖሚ ጥገኝነት መላቀቅና ውስጣዊ አንድነታችን ማጠናከር እንደሚገባም አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም