በሲዳማ የዳያስፖራዎችን ቆይታ ያማረ ከማድረግ ባለፈ የኢንቨስትመንት አማራጮችን ለማስተዋወቅ ዝግጅት ተደርጓል

60

ሀዋሳ፤ ታህሳስ 14/2014(ኢዜአ) ወደ ሀገር ቤት የሚመጡ ዳያስፖራዎች በሲዳማ ክልል የሚኖራቸውን ቆይታ ያማረ ከማድረግ ባለፈ የኢንቨስትመንት አማራጮችን ለማስተዋወቅ ዝግጅት መደረጉን የክልሉ ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ገለጸ፡፡

የቢሮው ኃላፊ አቶ ጃጎ አገኘሁ በክልሉ ዳያስፖራውን ለመቀበል በተደረገው ዝግጅት ዙሪያ ዛሬ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥተዋል።

ዳያስፖራው ለሀገራዊ ጥሪው በጎ ምላሽ መስጠቱ  ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ እንዳለው ነው ያመለከቱት።

አንዳንድ ምዕራባውያን ሀገራትና መገናኛ ብዙሃኖቻቸው ኢትዮጵያ ሠላም እንዳልሆነች በየአቅጣጫው በማራገብ ዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ለማደናገር የሚያደርጉትን ጥረት እንደሚቀለብስ ገልጸዋል፡፡

በኢኮኖሚውም ዘርፍ የውጭ ምንዛሪ እጥረትን ለማቃለልና የቱሪዝም ኢንዱስትሪውን በማነቃቃት ድርሻው የጎላ መሆኑንም ተናግረዋል።

አሸባሪው ህወሓት በከፈተው ጦርነት ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች የሚያደርጉት ድጋፍም የኢትዮጵያውያንን የዳበረ ማህበራዊ እሴት እንደሚያሳይም ኃላፊው አመልክተዋል።

ዳያስፖራው በክልሉ የሚኖራቸውን ቆይታ አይረሴና ያማረ ለማድረግ ከአገልግሎት ሰጪ ተቋማት እንዲሁም ከሚመለከታቸው የፌዴራልና የክልል አካላት ጋር እየተሰራ መሆኑንም አስታውቀዋል።

በክልሉ ያሉት እምቅ የኢንቨስትመንት አማራጮችን ለማስተዋወቅ ዝግጅት መደረጉን አቶ ጃጎ ገልጸዋል።

ክልሉ ለዳያስፖራው በዓለም አቀፍ ደረጃ በጣዕሙና በጥራቱ የሚታወቀውን ቡናውን እሴት ጨምሮ ለውጭ ገበያ በማቅረብ ያሉትን አማራጮች ያስተዋውቃል ብለዋል።

በቱሪዝም ኢንዱስትሪውም የሀዋሳ ሀይቅን፣ የሎካ አባያ ብሔራዊ ፓርክንና ሌሎች መስህቦችን  ለማስተዋወቅ መዘጋጀቱን አመላክተዋል።

ዳያስፖራዎች በክልሉ በሚኖራቸው ቆይታ ከሀዋሳ ሀይቅ ጋር የተያያዙ መዳረሻዎችንና የዓሣ ገበያን እንዲሁም በወንዶገነትና በይርጋለም የሚገኙ የፍል ውሃ መዝናኛዎችንና ሎጆችን እንደሚጎበኙ መመቻቸቱን  አቶ ጃጎ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ አረንጓዴ ወርቅ የሆነው ቡና በክልሉ ሕዝብ ውስጥ ያለውን ማህበራዊ ትስስር የሚያሳይ ከእሸት ቡና ለቀማ ጀምሮ ተፈልቶ እስከሚጠጣበት ድረስ ያለውን ሙሉ ሂደት የሚያሳዩ ትዕይንቶችም የዝግጅቱ አካል እንደሚሆኑ ነው ኃላፊው ያብራሩት፡፡

ዝግጅቱ የሲዳማን ብሎም የኢትዮጵያን ገፅታ በሚገነባ መልኩ ጎብኚዎቹ ምቾት፣ ሠላምና ደህንነታቸው ተጠብቆ እንደሚስተናገዱ የተቀናጀ እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም