አገር በቀል የኢኮኖሚ ለውጡ በጦርነቱ ከፍተኛ ጉዳት እንዳይደርስ አስተዋጽኦ አድርጓል

221

ታህሳስ 14/2014/ኢዜአ/ አገር በቀል የኢኮኖሚ ለውጥ መደረጉ በጦርነቱ ምክንያት ከፍተኛ ጉዳት እንዳይደርስ አስተዋጽኦ ማድረጉን የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ ገለጹ።

የአዲስ ወግ ውይይት”ሕልውናን መጠበቅ፣ ዕድገትን ማዝለቅ” በሚል ርዕስ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት  ተካሂዷል፡፡

ሚኒስትር አህመድ ሽዴ በውይይቱ ባለፉት ወራት ከፍተኛ የኢኮኖሚ ጉዳት ቢደርስብንም፣ ማክሮ ኢኮኖሚያችን በከፍተኛ ሁኔታ አልተዛባም ሲሉ ገልጸዋል።

ሚኒስትሩ በመድረኩ ባቀረቡት ሐሳብ አሸባሪው ህወሓት ኢትዮጵያ ላይ በከፈተው ጦርነት የደረሱ የኢኮኖሚ ጉዳቶችን አንስተዋል።

በጦርነቱ መካከል በአብዛኛው የአገሪቱ ክፍል የመንግሥት መዋቅሮች መደበኛ አገልግሎታቸውን  መቀጠላቸውንም ገልጸዋል።

የውጭ ግብይትና መደበኛ ሥራዎች በጥሩ ሁኔታ ተከውነዋል፣ ከሥራ ፈጠራ አንጻርም በርካታ ዕድሎች መኖራቸውን ጠቁመዋል።

የዕለት ደራሽ ዕርዳታ፣ ነጻ በሆኑ አካባቢዎች የመሠረተ-ልማት መልሶ ግንባታ፣ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ወደ መደበኛ ሥራቸው እንዲገቡ የማድረግ ሥራዎችም እየተሠሩ ነው ብለዋል ሚኒስትሩ።

አገራዊ ችግርን ለመፍታት ድህነትን መሻገር ይገባል ያሉት ሚኒስትሩ ለዚህም በኢኮኖሚው ዘርፍ ጠንካራ መሆን አማራጭ የሌለው እንደሆነም አክለዋል።

እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ አገር በቀል የኢኮኖሚ ለውጥ መደረጉ በጦርነቱ ምክንያት ከፍተኛ ጉዳት እንዳይደርስ አስተዋጽኦ አድርጓል።

የደረሰውን ጉዳት አጥንቶ መልሶ የማቋቋም በጀት መድቦ መሥራት ቀጣዩ እርምጃ መሆኑን ጠቁመው፤ የልማት አጋሮችና ኢትዮጵያዊያን ሁሉ መረባረብ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

የውይይቱ ታሳታፊዎች በጉዳዩ ላይ በሰነዘሩት ሃሳብ በኢኮኖሚ ራሳችንን መቻል ቀዳሚ ስራ መሆን አለበት ብለዋል።

በኢኮኖሚ ራስን መቻል ከውጭ ጫና ለመዳን የሚያግዝ መሆኑን በመጥቀስ።

ሕዝቡ በኢኮኖሚ መስክ ለመከላከያ ሠራዊትና ለተፈናቃይ ወገኖች እያደረገ ያለውን ድጋፍ ተቋማዊ በማድረግ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ማድረግ እንደሚገባም አስተያየት ሰጪዎቹ አመልክተዋል፡፡

ላጋጠመው አደጋ ምላሽ ለመስጠት እየተደረገ ያለው ርብርብ ታላቅ እና ከውጭ እርዳታ በላይ እንደሆነም ነው ያወሱት።

ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ በጦርነቱ የተጎዳውን ኢኮኖሚ ለማካካስ ብሎም መልሶ ለመገንባት ተጨማሪ በጀት የሚጠይቅ በመሆኑ በሚኒስቴሩ ተሰርቶ ረቂቁ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት መቅረቡን ገልጸዋል።

በቅርቡም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ የሚጸድቅና ወደ ስራ የሚገባ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡