በአሸባሪው ህወሓት ላይ የተመዘገበው ድል የኢትዮጵያዊነትን አይበገሬነት በተግባር ያሳየ ነው

66

ታህሳስ 14/2014 /ኢዜአ/ በአሸባሪው ህወሓት ላይ የተመዘገበው ድል የኢትዮጵያዊነትን አይበገሬነት በተግባር ያሳየ ነው ሲሉ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ ተናገሩ፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አዘጋጅነት የሚከናወነው አዲስ ወግ ዛሬ “ህልውናን መጠበቅ፣ ዕድገትን ማዝለቅ” በሚል ርዕስ ተካሂዷል፡፡

በመድረኩ ላይ የውይይት መነሻ ፅሁፍ ያቀረቡት የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ “በአሸባሪው ህወሓት ላይ ለተመዘገበው ድል ባለቤቱ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ነው" ብለዋል፡፡


ኢትዮጵያን ለማፍረስ ተነስቶ የነበረው አሸባሪው ህወሓት በኢትዮጵያውያን የጋራ ክንድ ተመትቶ እቅዱ መክሸፉን ያነሱት ሚኒስትሩ፥ የቡድኑ መጨረሻ ሽንፈት ሆኗል ነው ያሉት።


አሸባሪው ቡድን ሽንፈቱን ላለመቀበል የተለያዩ የሀሰት መረጃዎችን በማሰራጨት ላይ መሆኑን ጠቅሰዋል።


አሸባሪው በሥነ-ልቦና እና በፕሮፓጋንዳ ለማሸበር ሰፊ ዝግጅት ቢያደርግም በኢትዮጵያውያን የተባበረ ክንድ ዓላማው ሁሉ መክኗል ብለዋል።


በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተቀናጀ ዕቅድ፣ የአመራር ቅንጅት እንዲሁም በቴክኖሎጂ እና በሰው ኃይል በመዘጋጀት አሸባሪው ህወሓት በገባባቸው አካባቢዎች ሁሉ እንዲደመሰስ ተደርጓል ነው ያሉት።


ድሉ ሊመዘገብ የቻለው ኢትጵያውያን በሁሉም አውደ ግንባሮች ባደረጉት የድል አድራጊነት ዘመቻ መሆኑን ጠቅሰው በአሸባሪው ህወሓት ላይ የተመዘገበው ድል የኢትዮጵያዊነትን አይበገሬነት በተግባር ያሳየ ነው ብለዋል።


በውይይት መድረኩ ላይ የነበሩ ተሳታፊዎች የኢትዮጵያ ድል በኢትዮጵያውያን የጋራ ክንድ እውን ሆኗል ብለዋል።


ለድል አድራጊነቱ ኢትዮጵያውያን ያሳዩት አብሮነትና ትብብር በሌሎች መስኮችም ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባው ጠቁመዋል።


አሁን ያለንን የአሸናፊነት ስነ-ልቦና በመሰነቅ ለኢትዮጵያ ክብርና ሉዓላዊነት መከበር አብሮነታችን ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም