ወደ ካሜሮን የምንጓዘው ጥሩ ተፎካካሪ ለመሆን እንጂ ደርሶ ለመመለስ አይደለም

145


ታህሳስ 14/2014 /ኢዜአ/ ለአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ወደ ካሜሮን የምንጓዘው ጥሩ ተፎካካሪ ለመሆን እንጂ ደርሶ ለመመለስ አይደለም ሲሉ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ገለጹ።


33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በመጪው ጥር ወር በካሜሮን አስተናጋጅነት ይካሄዳል።

ከስምንት ዓመት በኋላ ለአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ የበቃችው ኢትዮጵያ የውድድሩ አስተናጋጅ ከሆነችው ካሜሮን፣ ኬፕቨርዴና ቡርኪናፋሶ ጋር መደልደሏ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በብሔራዊ ቡድኑ የአፍሪካ ዋንጫ ዝግጅትና ተሳትፎ ዙሪያ መግለጫ ሰጥቷል።

በመግለጫው የተገኙት የዋልያዎቹ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በአፍሪካ ዋንጫ የደረሰን ምድብ ጠንካራ ቢሆንም ወደ ያውንዴ የምናቀናው ጥሩ ተፎካካሪና አሸናፊ ለመሆን እንጂ ደርሶ ለመመለስ ብቻ አይደለም ብለዋል።

በዚህ ጨዋታ ጥሩ ተፎካካሪ ለመሆን የተሻለ ውጤት ያስመዘግባሉ ያሏቸውን ተጫዎቾች ማካተታቸውን ተናግረዋል።

በመሆኑም ከውድድሩ ቀን አስቀድመው ወደ ካሜሮን በመሄድ ዝግጅታቸውን ሲያደርጉ እንደሚቆዩ ነው የገለጹት።

ለአሰልጣኙ በውጭ የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያ ተጫዋቾች ለምን አልተመረጡም? ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄም የተጫዎቾችን አቅም የሚያሳይ በቂ ምስሎች ስላልተገኙና አቅማቸውን ለመሞከር የውድድር ጊዜው በመቃረቡ ማካተት እንዳልተቻለ ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዋና ፀሐፊ ባህሩ ጥላሁን፤ የፊታችን ቅዳሜ በስካይ ላይት ሆቴል ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት ለብሔራዊ ቡድኑ ሽኝት እንደሚደረግ ተናግረዋል።

የአፍሪካ ዋንጫ ከመጀመሩ ቀደም ብሎ ለብሔራዊ ቡድኑ አቅም መፈተሻ ቢያንስ ሁለት የወዳጅነት ጨዋታዎችን ለማድረግ መታቀዱንም ገልጸዋል።

መንግሥት ለብሔራዊ ቡድኑ ዝግጅትና ተሳትፎ 35 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉንም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም