የተፈናቀሉ ዜጎች መሠረታዊ የጤና አገልግሎት እንዲያገኙ በትኩረት መስራት ይገባል

56

ታህሳስ 14/2014/ኢዜአ/ በጦርነቱ ሳቢያ ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ዜጎች መሠረታዊ የጤና አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረግ እንደሚገባና ለዚህም እየተሰራ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር ገለጸ።

የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰን ጨምሮ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በአገር አቀፍ ደረጃ ተደራሽነቱን ለማስፋትና ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት በ2030 ለመስጠት የቃል ኪዳን ሰነድ ይፋ ሆኗል።

ዶክተር ሊያ፤ መንግሥት የእናቶችና ህፃናት ብሎም የአፍላ ወጣቶችን የስነ-ተዋልዶ ጤና ለማሻሻል እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ለቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት የሚያስፈልገውን በጀት የመመደብ፣ ጥራቱን የጠበቀ የጤናና  የምክር አገልግሎት እየተሰጠም ነው።

ግብዓቶችን ለማሟላትም እንዲሁ እየተሰራ መሆኑን፣ የቃል ኪዳን ሰነዱ ይፋ መሆንም የዚሁ ማሳያ እንደሆነ ተናግረዋል ዶክተር ሊያ።

ይሁንና የኮቪድ-19 ወረርሽኝ፣ በጦርነቱ ሳቢያ የበርካታ ጤና ተቋማት መውደምና መዘረፍ እንዲሁም በርካታ ዜጎች  ከመኖሪያቸው መፈናቀላቸው የጤናውን ዘርፍና ማኅበረሰቡን ፈተና ውስጥ የከተተ ነው ብለዋል።

በመሆኑም የተፈናቀሉ የማኅበረሰብ ክፍሎች መሠረታዊ የጤና አገልግሎት እንዲያገኙ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንና ይህም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ጠቁመዋል።

በሚኒስቴሩ የእናቶችና ህፃናት ጤና ዳይሬክተር ዶክተር መሰረት ዘላለም፤ ለተፈናቃይ ወገኖች ከአጋር አካላት ጋር በመሆን በተንቀሳቃሽ ተሽከርካሪና በጊዜያዊ ተቋማት የሕክምና አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።

በአዲስ አበባ ከሚገኙ ተቋማት ጋር ትስስር በመፍጠር የተጎዱ የጤና ተቋማትን ሥራ ለማስጀመር እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በአገር አቀፍ ደረጃ በ2030 ለመተግበር ዛሬ ይፋ የተደረገው የቤተሰብ ዕቅድ ቃል ኪዳን ከአገሪቷ የ10 ዓመት መሪ የልማት ዕቅዶች ጋር የተጣጣመ መሆኑ ተመላክቷል።

የኮቪድ-19 ወረርሽኝና ጦርነቱ የ2030 የቤተሰብ ዕቅድ ተግዳሮቶች መሆናቸውም ተገልጿል።

በቃል ኪዳኑ መሰረት የቤተሰብ ዕቅድ ተጠቃሚዎችን ቁጥር አሁን ካለበት 41 በመቶ በ2030 ወደ 55 በመቶ ለማሳደግ ታቅዶ እየተሰራ  ነው።

ከ18 ዓመት በታች ያሉ ሴቶች እርግዝናን አሁን ካለበት 13 በመቶ ወደ ሦስት በመቶ፣ የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት እየፈለጉ ማግኘት ያልቻሉትን ከ22 በመቶ ወደ 17 በመቶ ለመቀነስም ታቅዷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም