በበዓሉ ወቅት የዋጋ ንረትን ለመከላከል በመንግሥት የተዘጋጁ የገበያ አማራጮችን መጠቀም ይገባል

አዳማ ፤ ታህሳስ 14/2014(ኢዜአ) ለገና በዓል በሚኖረው የግብይት ወቅት የዋጋ ንረት ተፅዕኖን ለመከላከል ሸማቹ ህብረተሰብ በመንግሥት የተዘረጉ አማራጮችን እንዲጠቀም ተጠቆመ።

የኦሮሚያ ሴቶች ፌዴሬሽን   የገና በዓል ምክንያት በማድረግ በኦሮሚያ ክልል ከሚገኙ ዩኒዬኖችና የንግድ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ያዘጋጀው አውደ ርዕይና  ባዛር ዛሬ በአዳማ ከተማ ተከፍቷል።

የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ወይዘሮ አስካለ ለማ በወቅቱ እንዳሉት፤ በፍጆታ እቃዎችና ሸቀጦች ላይ ሊኖር የሚችለው የዋጋ ንረት መከላከል ይገባል።

በተለይ ከበዓሉ ጋር ተያይዞ የፍጆታ እቃዎች ላይ በሚከሰት የዋጋ ንረት ተፅዕኖ  ሸማቹ ህብረተሰብ እንዳይጎዳ አምራቹንና ሸማቹን ቀጥታ ለማገናኘት አውደ ርዕይና ባዛሩ መሰናዳቱን ገልጸዋል።

ህብረተሰቡ በስፋት የሚጠቀምበት ጤፍ፣ሽንኩርት፣ዘይት፣ስኳር፣የዳቦ ዱቄት፣የቤት ውስጥ እቃዎችን ጨምሮ ሸማቹ በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኝ ነው የተመቻቸው ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት ጦርነት በግንባር ብቻ አይደለም ያሉት ፕሬዚዳንቷ፤ በኢኮኖሚ ጦርነት ህዝቡን ለማማረር የሚደረገውን አፍራሽ እንቅስቃሴዎች ቦታ እንዳይኖራቸው ለመከላከል ፌዴሬሽኑ መንግስትን ለማገዝ የድርሻውን እየተወጣ መሆኑንም ተናግረዋል።

ከበዓሉ ጋር ተያይዞ ሊኖር የሚችለውን የዋጋ ንረት ተፅዕኖን ለመከላከል   ሸማቹ ህብረተሰብ በመንግስት የተዘረጉ አማራጮች  እንዲጠቀም  ጠቁመዋል።

የአዳማ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ሙሐመድ ጉዬ በበኩላቸው፤ በኢኮኖሚ ውስጥ እየተሰራ ባለው አሻጥር ሸማቹ ህብረተሰብ እየተጎዳ መሆኑን ጠቅሰው፤ የገና በዓል ምክንያት በማድረግ በተከፈተው በዛር ህብረተሰቡ የሚፈልገውን ሁሉ በአንድ ቦታ ማግኘት እንዲችል መመቻቸቱን ገልጸዋል።

ዛሬ በተጀመረው አውደ ርዕይና ባዛር  ላይ ከተገኙት ሸማቾች መካከል ወይዘሮ ከበቡሽ ገስጥ ፤ በዝግጅቱ ላይ የግብርና ምርቶች በቅናሽ ዋጋ እየገዙ መሆኑን ተናግረዋል።

ሽንኩርት ኪሎ 20 ብር እና ፓፓያ ኪሎ በ30 ብር መግዛታቸውን ጠቅሰው፤ ይህም ከባዘሩ ውጭ ካለው ዋጋ ጋር ሲነጻጻር ሽንኩርት በኪሎ የ10 ብር ፓፓያ ደግሞ የ20 ብር ቅናሽ እንዳለው አመልክተዋል።

ባዛሩ ገበያን ከማረጋጋትና ሸማቹ ህብረተሰብ ቀጥታ ከአምራቹ ጋር በማገናኘት ተጠቃሚ ያደረገ በመሆኑ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ነው ያሉት።

ወይዘሮ ቢታኒያ ጥሩነህም  በባዛሩ ጤፍ፣የዳቦ ዱቄት፣ዘይትና ስኳር ጨምሮ ሌሎችም ምርቶች  በተመጣጣኝ ዋጋ ማግኘታቸውን ገልጸዋል።

ጤፍ በየደረጃው ከገበያው ዋጋ ባነሰ ከ42 እስከ 46 ብር በኪሎ እየገዛን ነው፤ ገበያ ላይ ግን ከ48 እስከ 50 ብር እየተሸጠ ነው ብለዋል።

ለቀጣዮቹ  15 ቀናት በሚቆይው አውደ ርዕይና ባዛሩ ላይ  ከ150 በላይ  አምራች ዩኒዮኖች፣የንግድ ድርጅቶችና ነጋዴ ሴቶች ምርቶቻቸውን በማቅረብ  ይሳተፋሉ ተብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም