ግብራችንን በወቅቱ በመክፈል ሀገራዊ ግዴታችንን እየተወጣን ነው

85

ሆሳዕና ታህሳስ 14/2014 (ኢዜአ) የሚጠበቅብንን ግብር በወቅቱ በመክፈል ለሀገር ልማትና የብልጽግና ጉዞ ስኬታማነት የበኩላችንን እየተወጣን ነው ሲሉ በሀዲያ ዞን የንግዱ ማህበረሰብ አባላት አስታወቁ ።

በ2014 በጀት ዓመት የመጀመሪያዎቹ አራት ወራት 437 ሚሊዮን ብር  ገቢ መሰብሰቡን የሀዲያ ዞኑ ገቢዎች ባለስልጣን ጽህፈት ቤት  ገልጿል።

በሀዲያ ዞን ሆሳዕና ከተማ በሆቴል ንግድ ስራ የተሰማሩ አቶ ሙሴ አለው  ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት የደረጃ "ሐ"ግብር ከፋይ ሲሆኑ  የሚጠበቅባቸውን ከ30 ሺህ ብር በላይ ግብር በወቅቱ ከፍለዋል።

ቀደም ሲል ባገኙት ግንዛቤ መሠረት የሚጠበቅባቸውን ግብር በየዕለቱ ከሚሰጡት አገልግሎት በባንክ በመቆጠብ ካለምንም ችግር በወቅቱ ለመክፈል መቻላቸውን ተናግረዋል።

"ግብርን በወቅቱ መክፈል ለነገ የሚባል ጉደይ አይደለም" ያሉት አቶ ሙሴ እሳቸው ግብር በመክፈላቸው በሀገሪቱና በአካባቢያቸው በሚካሄዱ  የልማት ስራዎች የራሳቸውን አሻራ እንዳሳረፉ እንደሚሰማቸው ገልጸዋል።

አቶ ሙሴ ባስተላለፉት መልዕክት የንግዱ ማህበረሰብ  ካለማንም  ጎትጓችነት የሚጠበቅበትን ግብር በወቅቱ በመክፈል  ሀገራዊ ግዴታውን ሊወጣ  ይገባል።

በከተማዋ ሴች ዱና ቀበሌ  በእንጨትና ብረታ ብረት ስራ የተሰማራው ወጣት አማኑኤል በላቸው በበኩሉ 23 ሺህ ብር ግብር መክፈሉን ተናግሯል።

የግብርን ጥቅም በከተማዋ በተከናወኑ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት፣  የመጠጥ ውሃና መንገድ በመሳሰሉት መሠረተ ልማቶች  እያየን በመሆኑ እኔም ሆንኩ ጓደኞቼ ግብር ክፈሉ እስከምንባል ሳንጠብቅ ሃላፊነታችንን እየተወጣን ነው ብሏል።

"ይህም በሀገሪቱ የምንፈልገው ለውጥ እንዲመጣና የህዝብ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ ወሳኝ በመሆኑ ግብር በመክፈሌ ለልማት ስራዎች ስኬት  የዜግነት ግዴታዬን የተወጣሁ ያህል ይሰማኛል" ብሏል።

በዞኑ ሌሞ ወረዳ ሹርሞ ቀበሌ በእንሰሳት መኖ ማቀነባበር ስራ የተሰማሩትና የደረጃ "ለ" ግብር ከፋይ አቶ ምንተስኖት ብርሃኑ በበኩላቸው  ከሚያገኙት ገቢ ከ30 ሺህ ብር በላይ ዓመታዊ የመንግስትን ግብር በወቅቱ መክፈላቸውን ተናግረዋል።

"ግብርን በወቅቱ መክፈላቸው የዜግነት ግዴታቸውን በአግባቡ ከመወጣት ባሻገር በሀገሪቱ ለሚካሄደው  የልማትና  ብልጽግና  ጉዞ  ስኬታማነት የበኩሌን   ድርሻ እንደተወጣው ይሰማኛል" ብለዋል።

የሀዲያ ዞን ገቢዎች ባለስልጣን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መሳይ ተስፋዬ  በዞኑ በ2014 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ አመት ለመሰበሰብ ከታቀደው 479 ሚሊዮን ብር ገቢ ውስጥ 437 ሚሊዮን ብር   መሰብሰብን ገልጸዋል።

ከመደበኛና ማዘጋጃቤታዊ አገልግሎት የተሰበሰበው ገቢ ካለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ165 ሚሊዮን ብር በላይ ዕድገት ማሳየቱን ጠቅሰዋል።

የገቢ አሰባሰቡ ሀገሪቱ ካለችበት ነባራዊ ሁኔታና  በዞኑ ከተፈጠረው ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ አንጻር ሲታይ የተሻለ አፈጻጸም የተመዘገበበት እንደሆነ ጠቁመዋል።

እንደ ሃላፊው ገለፃ የዞኑ ኢኮኖሚ የሚያመነጨውን ገቢ አሟጦ ለመሰብሰብ ትኩረት ተሰጥቶ በየደረጃው በቅንጅት እየተሰራ ነው።

በዞኑ ከ15 ሺህ በላይ ህጋዊ ግብር ከፋዮች እንዳሉ ያመለከቱት ሃላፊው እስከ በጀት ዓመቱ መጨረሻ ከ1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሰራ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም