በአሸባሪ ቡድኑ ጥቃት የስነ-ልቦና ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎች የተመለከቱ ዘገባዎች ጥንቃቄ ይሻሉ

58

ታህሳስ 14 2014(ኢዜአ) በአሸባሪው ህወሓት ወረራ የስነ-ልቦና ጉዳት የደረሰባቸው ዜጎች የሚፈጠርባቸውን ጫና ለመቀነስ መገናኛ ብዙኃን በሚሰሩት ዘገባ ጥንቃቄ ሊያደርጉ እንደሚገባ የዘርፉ ባለሙያዎች አስገነዘቡ።

የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሚኒኬሽን መምህር ረዳት ፕሮፌሰር ጸጋነሽ ሙሉጌታ ጦርነት የምጣኔ ሃብት ጉዳቱ እንዳለ ሆኖ የስነ-ልቦና ጉዳቱ ከፍተኛ ነው ይላሉ።

አሸባሪው የህወሓት በአገርና በሕዝብ ላይ የፈጸመውንም በደል መገናኛ ብዙኃን በተደራጀ መንገድ የማቅረብ ኃላፊነት እንዳለባቸው ገልጸው በዚህ ረገድ የጦርነቱን ተጎጂዎች የሕይወት ታሪክና ያጋጠማቸውን ችግር ሲዘግቡ በጥንቃቄ መሆን እንዳለበት አስገንዝበዋል።

"ዘገባዎችን የሚያቀርቡበት ሁኔታ ተጎጂዎቹ በቀጣይ የሚጀምሩትን አዲስና የግል ሕይወታቸው ላይ እንዲሁም ማኅበራዊና አገራዊ ጉዳዮች ላይ ተጽዕኖ በማይፈጥር መልኩ ሊሆን ይገባል" ነው ያሉት።

ዜጎች በሽብር ቡድኑ የደረሰባቸውን የስነ-ልቦና እና አካላዊ ቁስል እንደሚሽር፣ ነገም የተሻለ ሕይወት እንዳለ በሚያሳይ መልኩ መሆን እንዳለበትም ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል የወደሙ የጤና ተቋማት፣ ትምህርት ቤቶች፣ የኢንደስትሪ ማዕከላትና ሌሎች መሰረተ ልማቶችን ለዓለም ማሳየት ተገቢ ቢሆንም፤ በዘገባዎች መልሶ መገንባትን እና ተስፋን ማሳየት ይገባልም ብለዋል።

በጦርነት ወቅት የሚተገበሩ የተግባቦት ስትራቴጂዎችን በመጠቀም ማኅበረሰቡን የማቀራረብ ሥራ ትኩረት እንዲሰጠውም አመልክተው መገናኛ ብዙኃን አገርን መልሶ ለመገንባት እያንዳንዱ ዜጋ የሚጠበቅበትንና ሊያደርግ የሚችለውን በሚያመላክቱ ዘገባዎች ላይ ሊያተኩሩ እንደሚገባም አክለዋል።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያ ሴቶች ማኅበር ቦርድ ሊቀመንበር ሶሎሜ ደስታ በበኩላቸው፤ መገናኛ ብዙኃን ተጎጂዎች ከደረሰባቸው የህሊና ቁስል የሚያገግሙበትንና መልሰው የሚቋቋሙበትን መንገድ ማመላከት ይገባቸዋል ብለዋል።

ጋዜጠኞች ለተጎጂዎች የሚያቀርቧቸው ጥያቄዎችና የሚጠቀሟቸው ቃላት ላይ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባቸው ሙያተኞቹ መክረው በጦርነት ወቅት ከሚያጋጥሙ ውስብስብ ሁኔታዎች መካከል የአዕምሮ ቁስለት /ትራውማ/ አንዱ መሆኑንና አሸባሪው ህወሓት የፈጸማቸው የጅምላ ግድያና የሴቶች መደፈር ተጽዕኖው ከባድ እንደሆነ ጠቅሰዋል።

ይህንን ለማከም የስነ-ልቦናና የማኅበራዊ ሳይንስ ባለሙያዎች በግለሰብና በማኅበረሰብ ደረጃ መሥራት እንደሚጠበቅባቸው አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም