ዘመቻ ለሕብረ ብሔራዊ አንድነት የመጀመሪያውን ግብ በማሳካት ተልዕኮውን አጠናቀቀ

238

ታህሳስ 14 ቀን 2014 (ኢዜአ) በዘመቻ ለሕብረ ብሔራዊ አንድነት የተካሄደው የኢትዮጵያን ሕልውና የማስጠበቅ ዘመቻ የመጀመሪያውን ግብ በማሳካት ተልዕኮውን ማጠናቀቁን መንግስት አስታወቀ።

የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ሀላፊ ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ዛሬ በሰጡት መግለጫ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ መሪነት በተካሄደው ዘመቻ ለሕብረ ብሔራዊ አንድነት ወራሪውና አሸባሪው የህወሃትን ሃይል እንዲበታተንና እንዲደመሰስ ማደረጉን አስታውቀዋል።

ዘመቻው ወራሪው ሃይል እንዲበታተንና እንዲደመሰስ ከማድረግ በተጨማሪ የዘረፈውን ይዞ እንዳይወጣ ማድረጉንና ሳይወድ በግድ እጁን እንዲሰጥ ማድረጉን ገልጸዋል።

በዘመቻ ለሕብረ ብሔራዊ አንድነት አሸባሪውን ህወሃት ዳግም ለኢትዮጵያ ስጋት እንዳይሆን የማድረግ ተልዕኮ እንደነበረው አንስተው፤ ከአፋር ክልል እንዲሁም በአማራ ክልል ምስራቅ ዞኖች ሙሉ በሙሉ እንዲወጣና አካባቢው ነጻ እንዲሆን መደረጉን ተናግረዋል።

በዚህ ዘመቻ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን አሸንፈዋል ያሉት ሚኒስትሩ የመከላከያ ሰራዊት፣ አየር ሃይል፣ ኮማንዶና ሜካናይዝድ ጦሩ በኢትዮጵያ በታሪክ ወርቃማ ሆኖ የሚጻፍ ታሪክ ፈጽመዋል፣ የአማራና የአፋር የጸጥታ ሃይሎችም የራሳቸውን ከፍተኛ ተጋድሎና አኩሪ ድርሻ የተወጡበት ነበር ብለዋል።

የመላው ህብረተሰብ ድጋፍም የደጀንንት ሚናውን እንደ ጥንቱ መሆኑን ያሳየበት ነበርም በማለት አብራርተው ወቅታዊ የጠላት ሁኔታ ግምገማ የሚያሳየው የጠላት የመሻትና የማድረግ ሃይል ክፉኛ ተመቷል።