የኢትዮጵያን ጥሪ ተቀብለው ወደ አገር ቤት የሚመጡ እንግዶችን "አርሂቡ" ብለን ልንቀበላቸው ተዘጋጅተናል

81

አዲስ አበባ፣  ታህሳስ 14/2014(ኢዜአ) የኢትዮጵያን ጥሪ ተቀብለው ወደ አገር ቤት የሚመጡ እንግዶችን "አርሂቡ" ብለን ልንቀበላቸው ተዘጋጅተናል ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው አስጎብኚ ድርጅቶች ገለጹ።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ጥሪ ተቀብለው በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያዊያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች "ታላቁ ጉዞ ወደ አገር ቤት" በሚል በፈረንጆቹ አዲስ ዓመት ዋዜማ የሰው ዘር እና የቡና መገኛ ወደ ሆነችው ኢትዮጵያ ለመምጣት ተሰናድተዋል።

ኢትዮጵያ ታይቶ የማይጠገብ፣ ተሰምቶ የማይሰለች በበርካታ መስህብ የታደለች ዓመቱን ሙሉ ጸሃይ የማይጠፋባት የምድራችን ልዩ አገር መሆኗን መናገር ይቻላል።

ኢትዮጵያ ከላልይበላ እስከ ኮንሶ፣ ከኤርታሌ እስከ ድንቅ መስህቦቿ ራስ ደጀን፣ ባሌ ተራሮችን ጨምሮ ሌሎችም ፓርኮች ደጋግመው ቢመለከቱት የማይሰለች ሃብት አላት።

በርካታ የቱሪስት መዳረሻዎችና መዝናኛዎች ያሉባት አዲስ አበባን ጨምሮ የክልል ከተሞችና የገጠር መዳረሻዎች ሁሉ ኢትዮጵያ የምትገለጽባቸውና የምትታወቅባቸው ታይቶና ተነግሮ የማይሰለች ድንቅ ስጦታ ተችሯታል።

ሃይማኖታዊና ህዝባዊ በአላት የሚደምቅባት፣ የሙዚቃና ኪነ ጥበብ ድንቅ ትውፊት የሚታይባት፤ በስፖርት ከአበበ ቢቄላ እስከ አረንጓዴው ጎርፍ የዓለም ስመጥር አትሌቶች መገኛም ነች።  

ከብዙው በጥቂቱን የጠቀስንላትን አገር የኢትዮጵያ ወዳጆችና ከማህጸኗ የበቀሉ ልጆቿ በቀረበላቸው ጥሪ መሰረት በእንግድነት ለመገኘት ተዘጋጅተዋል።

ታዳሚዎችን በመቀበል ያማረ፣ የሰመረ ቆይታ እንዲኖራቸው ተዘጋጅተው ከሚጠብቁ ተቋማት መካከል የቱሪዝም ዘርፍ ተዋኒያን ይጠቀሳሉ።

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉ አስጎብኚ ድርጅቶች፤ የኢትዮጵያን ጥሪ ተቀብለው ወደ አገር ቤት የሚመጡ እንግዶችን "አርሂቡ" ብለን ልንቀበላቸው ተዘጋጅተናል ሲሉ አረጋግጠዋል።

የግራንድ ሆሊደይስ ኢትዮጵያ አስጎብኚ ድርጅት ስራ አስኪያጅ አቶ ደሳለ ምትኩ፤ እንግዶቻችንን በመቀበል ኢትዮጵያ አንዳንድ የውጭ ሚዲያዎች ከሚያሰራጩባት ሀሰተኛ መረጃ በተቃራኒው ሰላም መሆኗን በተግባር ለማሳየት ተዘጋጅተናል ብለዋል።

የአገርና ወገን አለኝታነታቸውን ለማሳየት ወደ አገር ቤት የሚገቡ እንግዶችም የኢትዮጵያን ታሪክ፣ ባህል፣ ቅርስ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ መስህቦችን ለማሳየት ተዘጋጅተናል ነው ያሉት። 

የአንድል ኢትዮጵያ አስጎብኚ ድርጅት ዋና ስራ አስኪያጅ መሐሪ መሰለ፤ የታላቁ የኢትዮጵያዊያን ወደ አገር ቤት ጉዞ የተቀዛቀዘውን የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ለማነቃቃት ከፍተኛ ፋይዳ እንደሚኖረው ገልጸዋል።

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ አሁናዊ ተጨባጭ ሁኔታን ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በማሳየት በኢትዮጵያ ገጽታ ግንባታ ረገድም ትልቅ አጋጣሚ ይፈጥራል ነው ያሉት።

በዚህም የጉዞውን አገራዊ ፋይዳ በመረዳት ድርጅታቸው በአገራዊ ስሜት እንግዶችን ከአየር ማረፊያ ተቀብሎ በቆይታቸውም ደስ የሚያሰኝ አገልግሎት ለማቅረብ ዝግጅት ማድረጉን አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ የአስጎብኝዎች ማህበር የቦርድ አባል አቶ ቦጋለ አባይ፤ ለእንግዶች ኢትዮጵያዊ አቀባበልና መስተንግዶ ለማቅረብ የሚያስችል ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል።

እንግዶች በየትኛውም አካባቢ ሲንቀሳቀሱ ሰላምና ደህንነታቸው ተጠብቆ በፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት በተመጣጣኝ ዋጋ አገልግሎት የሚያገኙበት የአሰራር ስርአት ተመቻችቷል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም