የተፈናቀሉ ወገኖችን መልሶ ለማቋቋም እየተደረገ ያለውን ጥረት እንደግፋለን—ባለሃብቶች

173

መተማ ፣ ታህሳስ 14/2014(ኢዜአ) መንግስት በአሸባሪው ህወሃት ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ወገኖችን መልሶ ለማቋቋም እያደረገ ያለውን ጥረት እንደግፋለን ሲሉ በአማራ ክልል ባለሃብቶች አስታወቁ።

ባለሀብቶቹ በዛሬው እለት በምዕራብ ግንባር ለሚገኙ የመከላከያ ሰራዊትና ለሌሎች የጸጥታ ሃይሎች ከ1ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው የምግብና ቁሳቁስ ድጋፍ አድርገዋል።

የባለሃብቶች ጥምረት ተወካይ አቶ ጉንባ ብርሌ በምእራብ ጎንደር ዞን ገንዳውሃ ከተማ ድጋፉን ባስረከቡበት ወቅት እንዳሉት ህዝብን ለመበደልና ሀገር ለማፍረስ የተነሳው የሽብር ቡድን በመላው ኢትዮጵያውያን ትብብር አላማው ከሽፏል።

ባለሀብቶች በግንባር በመገኘት የሀገርን ሉአላዊነት ለማስከበር ከወራሪው ሀይል ጋር እየተፋለመ ላለው ጥምር የፀጥታ ሃይል ከ1 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው የምግብና ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም በሌሎች የአማራና የአፋር ክልል ግንባሮች በመገኘት ከ800 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ምግብና ቁሳቁስ ድጋፍ መደረጉን አስታውሰዋል።

የሽብር ቡድኑ ሙሉ በሙሉ ተደምስሶ የሀገሪቱ ሰላም እስኪረጋገጥ ድረስ ለሠራዊቱና ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎች መልሶ ለማቋቋም ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ጠቁመዋል።

የምዕራብ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪና የኮማንድ ፖስት ሰብሳቢ አቶ ደሳለኝ ጣሰው በበኩላቸው “ዛሬ የተደረገው ድጋፍ ለፀጥታ ሃይሉ ተጨማሪ አቅም ይፈጥራል” ብለዋል።

”የሽብር ቡድኑና ተባባሪዎቹ በዞኑ ስምንት ጊዜ ያክል ጥቃት ለማድረስ ሞክረዋል” ያሉት ዋና አስተዳዳሪው፤ “በጀግኖቹ የፀጥታ ሃይሎችና በህዝቡ ጀግንነት ህልማቸውን ቅዠት ማድረግ ተችሏል” ሲሉ ተናግረዋል።

የዞኑ ህዝብ ለህልውና ዘመቻው እስካሁን በጥሬ ገንዘብ ብቻ ከ114 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉን አቶ ደሳለኝ አስታውቀዋል።