የትግራይ ህዝብ አሸባሪውን ህወሃት ከጫንቃው ላይ ማውረድ አለበት

261

አዳማ፤ ታህሳስ 14/2014 (ኢዜአ)የትግራይ ህዝብ አሸባሪው የህወሃት ቡድንን በቃህ በማለት ከጫንቃው ላይ ማውረድ አለበት ሲሉ በአዳማ ከተማ የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች አስታወቁ።

በአዳማ የአባገዳ ክፍለ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ኢማን ሙሐመድ፤ አሻባሪው ህወሃት ለራሱ ጥቅም ሲል  የትግራይ ህዝብን በተለይም ወጣቱን  እያስጨረሰ ያለ ከሃዲ ቡድን ነው ብለዋል ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት።

የትግራይ እናቶችና አባቶች ልጆቻችንን አምጡ ብለው መጠየቅ እንዳለባቸው ያመለከቱት ወይዘሮ ኢማን፤  አሸባሪው ህወሃት በዜጎች ላይ እየፈፀመ ያለው ዘግናኝ ተግባር በዘመናችን አይተን አናውቅም ነው ያሉት።

ይሄ ቡድን ዜጎችን በተከበሩበት ሀገር ማዋረዱን ፤  የእምነት ተቋማትን ማውደሙን፣ እርጉዝ ሴቶችን ሳይቀር የሚደፍር ጨካኝ መሆኑን በማውሳት ድርጊቱን ኮንነዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በግንባር ተገኝተው ሠራዊቱን በመምራት እያስመዘገቡት ባለው ድል የትግራይ ህዝብ በቅርቡ ከአፋኙ ሃይል ነፃ እንደሚወጣ ተስፋ እንዳላቸውም ገልጸዋል።

የሀገራችንን ዘርፈ ብዙ ችግር ለማስተካከል መንግስት በአሸባሪው ህወሃት ላይ እያስመዘገበ ያለውን ድል አጠናክሮ መቀጠል አለበት ያሉት ደግሞ ሌላው በአዳማ ከተማ ኢሬቻ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ዮናስ ገብረኪሮስ ናቸው።

የአሸባሪው ቡድን የጥፋት ድርጊት  ተቀባይነት የሌለው እኩይ ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።

የትግራይ ወጣቶች ሠርተው መለወጥ በሚችሉበት ግዜ ለአንድ ቡድን ዓላማ ማስፈፀሚያ እየሞቱ ነው ያሉት አቶ ዮናስ፤  የትግራይ እናቶች አሸባሪው የህወሃት ቡድን በቃህ በማለት ከጫንቃው ላይ ማውረድ እንዳለበት ነው ያመለከቱት።

የዚህ ቡድን እኩይ ተግባር  ሀገርን ለማፍረስ ያለመ ነው ያሉት አቶ ዮናስ፤ አሸባሪውን ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ጋር በመሆን ለመታገል ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በአካባቢ ሰላምና ጸጥታ አጠባበቅ ላይ  በመሳተፍ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እያደረጉ እንደሚገኙ አስታውቀዋል።

የደምበላ ክፍለ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ አበባ ሃይሉ  በበኩላቸው፤ አሸባሪው ህወሃት በአማራና አፋር ክልሎች  በህፃናት፣አረጋዊያን፣እናቶችና አባቶች ብሎም በሀገር ሀብት ላይ ያደረሰው ጥፋት የሚወገዝ መሆኑን ተናግረዋል።

የትግራይ ህዝብ አሸባሪው ህወሃትን ሰላም ነው የምንፈልገው በቃህ ሊለው ይገባል ብለዋል።

የትግራይ ክልል ማህበረሰብ በተለይ ወጣቱ የ”በቃ” ዘመቻ  ንቅናቄ መቀላቀል አለበት ያሉት ወይዘሮ አበባ፤ በእሳቸው በኩል ኢትዮጵያን ለማዳን እየተካሄደ ባለው ትግል በደጀንነት በመደገፍ የድርሻቸውን እየተወጡ መሆናቸውን ገልጸዋል።