የትምህርት ዘርፉን ውጤታማ ማድረግ የልማትና ሰላም ጉዳዮችን ማሳካት ነው

62

ሃዋሳ፣ ታህሳስ 14/2014(ኢዜአ) የትምህርት ዘርፉን ውጤታማ ማድረግ የልማትና ሰላም ጉዳዮችን ማሳካት ስለሆነ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ በቅድሚያ እንደሚሰራ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ አስታወቁ።

የመጀመሪያው የሲዳማ ክልል የትምህርት ጉባኤ ዛሬ በሃዋሳ ከተማ ተጀምሯል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ደስታ ሌዳሞ በዚህ ወቅት እንዳሉት "የክልሉንም ሆነ የአገሪቱን እድገትና ልማት በዘላቂነት ለማረጋገጥ ብቃት ያለው የተማረ የሰው ሀይል ማፍራት ያስፈልጋል፤ ለዚህም በየደረጃው የትምህርት ጥራትን ማስጠበቅ ወሳኝ ነው"።

መንግስት በትምህርት ዘርፍ ስር ነቀል ለውጥ ለማምጣት አዲስ የትምህርት ፍኖተ ካርታ በማዘጋጀትና  አስፈላጊውን ግብዓት በሟሟላት ወደ ትግበራ ሂደት መግባቱን አመልክተዋል።

"በክልሉ የትምህርት ዘርፉን ውጤታማ ማድረግ የልማትና ሰላም ጉዳዮችን ማሳካት ነው" ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ ይህንኑ ታሳቢ በማድረግ የትምህርት ጥራትን ማስጠበቅ ቀዳሚ አጀንዳ ሆኖ እንደሚሰራ አስታውቀዋል።

በተለይ ብቃት ያለው የትምህርት ሴክተር ለመፍጠር መምህራንን ጨምሮ የባለድርሻ አካላት ተሳትፎና ሚና የላቀ መሆኑን ያስረዱት ርዕሰ መስተዳደሩ "በክልሉ በየደረጃው ያሉ መምህራንን አቅምና ብቃት ለማሳደግ የተለያዩ ስልቶች በመዘርጋት ተፈጻሚ ለማድረግ ታቅዷል ብለዋል።

የትምህርት ሴክተሩ ተዋናዮችና ባለድርሻ አካላት የአገሪቱ የነገ ዕጣ ፈንታ የሚወስነው በዕውቀትና በክህሎት የተካነ የሰው ሃይል ማፍራት ሲቻል መሆኑን ተረድተው ለዘርፉ መበልጸግ በሙሉ አቅማቸው እንዲረባረቡም አሳስበዋል።

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የትምህርት ቢሮ ሃላፊ አቶ በየነ በራሳ በበኩላቸው፣ ጉባኤው የትምህርት ጥራት ለማረጋገጥ እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎች አፈጻጸም፣ በሂደት ባጋጠሙ ተግዳሮቶችና ቀጣይ ግቦች ላይ አተኩሮ የሚመክር መሆኑን ተናግረዋል።

"የትምህርት ዘርፍ ውጤታማነት የሚለካው ብቃት ያለው፣ መልካም ስነ ምግባር የተላበሰና ራዕይ ያለው የሰው ሃይል ማፍራት ሲቻል ነው" ያሉት አቶ በየነ፣ ለእዚህም በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይ የመምህራን፣ የተማሪዎችና የትምህርት አመራር ብቃትና ተነሳሽነት ላይ የሚስተዋለውን ክፍተት ለማሻሻል ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ ነው ያመለከቱት።

በክልሉ የሚገኙ አብዛኞቹ ትምህርት ቤቶች ደረጃቸውን የጠበቁ እንዳልሆኑ አቶ በየነ ጠቁመው፣ "የተቋማቱን ደረጃ በማሻሻል ሳቢና ምቹ ለማድረግ የሁሉንም ድጋፍና ተሳትፎ ይጠይቃል" ብለዋል።

ለሁለት ቀን በሚቆየው ጉባዔ ላይ ከክልሉ የተውጣጡ ባለድርሻ አካላትና የሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ምሁሯን እየተሳተፉ ነው።

በሲዳማ ክልል በዚህ ዓመት  ከ1 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ከ1ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ትምህርታቸውን እየተከታተሉ መሆኑን ከቢሮው የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም