የአሸባሪዎቹ ህወሃትና ሸኔ ተላላኪዎች በድሬዳዋ መሸሸጊያ እንዳያገኙ ወጣቶች ነቅተው እየጠበቁ ይገኛሉ

185

ድሬዳዋ፣ ታህሳስ 14 ቀን 2014 (ኢዜአ) የአሸባሪዎቹ ህወሃትና ሸኔ ተላላኪዎች በድሬዳዋ አስተዳደር መሸሸጊያ እንዳያገኙ ወጣቶች ነቅተው እየጠበቁ መሆናቸውን ተናገሩ።

የድሬዳዋ አስተዳደር ወጣቶች ተደራጅተው ፈረቃ በማውጣት ከጸጥታ ሃይሎች ጋር ተቀናጅተው አካባቢያቸውን በመጠበቅ የደጀንነት ሃላፊነታቸውን በመወጣት ላይ እንደሚገኙ አመልክተዋል።

ተደራጅተው የአካባቢን ጸጥታ በማስጠበቅ የድርሻቸውን እየተወጡ ከሚገኙት ወጣቶች መካከል ኢዜአ ያነጋገራቸው ወጣት አብዲ አህመድ፣ ወጣት መሳይ ጌታቸው፣  ወጣት ምህረት አክሊሉ እና ወጣት መቅደስ ፀጋዬ አካባቢያቸውን ነቅተው በመጠበቅ የደጀንነት ተግባር እየፈጸሙ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

በተለይም የአሸባሪዎቹ ህወሃትና ሸኔ ተላላኪዎች በድሬዳዋ መሸሸጊያ እንዳያገኙ በንቃት እየጠበቁ ስለመሆናቸው ተናግረዋል።

ድሬዳዋ የአሸባሪዎቹ ህውሃትና የሸኔ ተላላኪዎች ምሽግ እንዳትሆን ከፀጥታ አካላት ጋር ተቀናጅተን በቀንና በምሽት እየሰራን ነው ብለዋል፡፡

በፈረቃ ተደራጅተው እየጠበቁ የሚገኙት ወጣቶቹ፤ የከተማዋን ሰላም ለማደፍረስ የሚሯሯጡ አካላትን በጥብቅ ፍተሻ እየተቆጣጠሩ እንደሆነ አመልክተዋል።

አገርንና አካባቢን መጠበቅ የሁሉም ኃላፊነት እንደሆነ የተናገሩት ወጣቶቹ፤ የቀድሞ የድሬዳዋ ህብረትና አንድነትን ለመመለስ እየሰራን እንገኛለን ብለዋል።

አሸባሪው ህወሃት በአማራና አፋር ክልሎች በወረራ በገባበት ወቅት ያደረሰውን ውድመትና የወገኖች መፈናቀል ላይ የሚሰሩ መልሶ የማቋቋም ተግባር ላይ የድርሻቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።

የድሬዳዋ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽን የለውጥና የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮማንደር ገመቹ ካቻ የድሬዳዋ ወጣቶች አገርን በሁሉም ግንባር ለማዳን አርአያነት ያለው ተግባር እየፈጸሙ እንደሚገኙም ጠቁመዋል።