የሌላ አገር ዜግነት ያላቸው ትውልደ ኢትዮጵያውያን በአዲስ አበባ በሚገኙ የየአገሮቻቸው ኤምባሲዎች ተገኝተው የኢትዮጵያን እውነት እንዲያስረዱ ይደረጋል

90

ታህሳስ 14/2014/ኢዜአ/ የሌላ አገር ዜግነት ያላቸው ትውልደ ኢትዮጵያውያን በአዲስ አበባ በሚገኙ የየአገሮቻቸው ኤምባሲዎች ተገኝተው የኢትዮጵያን እውነት እንደሚያስረዱ 'ዲፌንድ ኢትዮጵያ ዩሮፕ' የተሰኘው ግብረ ሃይል አስታወቀ።

ለኢትዮጵያዊያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያዊያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች በቀረበው ወደ አገር ቤት እንግባ ጥሪ መሰረት ከ12 የአውሮፓ አገራት እንግዶች ወደ አገር ቤት እንደሚመጡም ግብረ ሃይሉ ገልጿል።

የ'ዲፌንድ ኢትዮጵያ ዩሮፕ' ግብረ ሃይል አስተባባሪ አቶ ዘላለም ጌታሁን፤ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ያቀረቡትን ጥሪ ተከትሎ በርካቶች ወደ አገር ቤት ለመግባት በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በዚህ መርሃ ግብር ላይ ለመገኘት ከሚመጡት እንግዶች መካከል ከሚመጡበት አገር ዜግነት ያላቸው ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በአዲስ አበባ በሚገኙ የየአገራቱ ኤምባሲዎች ተገኝተው የኢትዮጵያን እውነት እንደሚያስረዱ ተናግረዋል።

እንግዶቹ ወደ ትውልድ አገራቸው ሲመጡ በዜግነት የሚኖሩባቸውን አገራት ኤምባሲዎች ስለ ኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ እንደሚያነጋግሩና የኢትዮጵያን እውነት እንደሚያስረዱ አቶ ዘላለም ገልጸዋል።

በተለይ ኢትዮጵያን በተመለከተ የተዛባ አቋም ከያዙ አገራት የሚመጡ እንግዶች የአገሮቹን  አምባሳደሮች በማነጋጋር በኢትዮጵያ ላይ እየተከተሉ ያለውን ትክክለኛ ያልሆነ አካሄድ እንደማይቀበሉት በማሳወቅ፤ የያዙትን ፖሊሲ በማስተካከል ከኢትዮጵያ ጋር በመከባባር ላይ የተመሰረተ ግንኙነት ሊኖራቸው እንደሚገባ እናስረዳቸዋለን ብለዋል።

ኢትዮጵያ ከአገራቱ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት ማጠናከር በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ ከአምባሳደሮቹ ጋር እንደሚመክሩ አመልክተዋል።

ትውልደ ኢትዮጵያውያኑ የዲፕሎማሲ ስራውን በማከናወን ኢትዮጵያ የጣለችባቸውን አገራዊ ግዴታ እንደሚወጡም ነው አቶ ዘላለም ያስረዱት።

'ዲፌንድ ኢትዮጵያ ዩሮፕ' በእንግሊዝ፣ አየርላንድ፣ ጣልያን፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ስዊዘርላንድ፣ ቤልጂየም፣ ስዊድን፣ ኖርዌይ፣ ስፔን፣ ቼክ ሪፐብሊክና ኔዘርላንድ እየተንቀሳቀሰ ሲሆን ወደ አገር ቤት የሚደረገውን ጉዞ በማስተባበር ላይ ይገኛል።

ለኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጥሪውን የተመለከቱ መረጃዎችን የመስጠት ተግባር እየተከናወነ እንደሚገኝና የዝግጅት ስራዎችም መጠናቀቃቸውን አቶ ዘላለም አመልክተዋል።

እንግዶቹ ወደ አገር ቤት  በሚመጡበት ወቅት የተለያዩ ምርቶችን ከአገር ውስጥ በመግዛት ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ድጋፍ ለማድረግ መዘጋጀታቸውንም ጠቁመዋል።

ዳያስፖራዎቹ የሕክምናና ምህንድስና ባለሙያዎች፣ አስተማሪዎችና በሌሎች የሙያ መስኮች የተሰማሩ በመሆናቸው ወደ ኢትዮጵያ በሚመጡበት ጊዜም ባላቸው ሙያ አገራቸውን እንደሚያገለግሉ ተናግረዋል።

አሸባሪው ሕወሓት በጤና ተቋማት ያደረሰውን ዝርፊያና ውድመት ተከትሎ የተከሰተውን የጤና ቁሳቁስ እጥረት ለመቅረፍ ዳያስፖራዎቹ በጤና ሚኒስቴር የተጠየቁ የሕክምና እቃዎችን ወደ አገር ቤት ይዘው እንደሚመጡ ነው አቶ ዘላለም የገለጹት።

በሽብር ቡድኑ ወረራ ምክንያት ለተፈናቀሉ ዜጎች ድጋፍ እንደሚደረግም ጠቁመዋል።

ከ12 አገራት የሚመጡ ዳያስፖራዎች ያላቸውን ገንዘብ ወደ ኢትዮጵያ ይዘው ሲመጡ ለውጪ ምንዛሬ  ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋል ያሉት አቶ ዘላለም በዚህ ረገድም ገንዘቡን በሕጋዊ መንገድ ብቻ በመመንዘር ኢትዮጵያን ለመደገፍ እንደተዘጋጁ አመልክተዋል።

ወደ ኢትዮጵያ ከሚመጡ ዳያስፖራዎች መካከል በኢንቨስትመንት መስክ ለመሰማራት ፍላጎት ያላቸው ዜጎች እንደሚገኙበት ገልጸዋል።

ዳያስፖራዎች በኢንቨስትመንት ዘርፍ መሰማራት የሚችሉባቸውን አማራጮች ለይተው ከሚመለከታቸው የመንግስት ባለድርሻ አካላት ጋርም ምክክር እንደሚያደርጉ ጠቁመዋል።

'ዲፌንድ ኢትዮጵያ ዩሮፕ' የተሰኘው ግብረ ሃይል ኢትዮጵያ እንዳትረጋጋ ከሚሰሩ የውስጥና የውጭ ጠላቶች ኢትዮጵያን መጠበቅና መከላከል አላማ በማድረግ የሚሰራ ጥምረት ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም