አንዳንድ የውጭ ሚዲያዎች በኢትዮጵያ ላይ የሃሰት መረጃ ያሰራጩትን ያክል ለእውነታና ሰብአዊነት ደንታ ቢስ ሆነው ታይተዋል

69

አዲስ አበባ ታህሳስ 14 ቀን 2014 (ኢዜአ) አንዳንድ የውጭ ሚዲያዎች በኢትዮጵያ ላይ የሃሰት መረጃ ያሰራጩትን ያክል ለእውነታና ሰብአዊነት ደንታ ቢስ ሆነው መታየታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በሳምንታዊ መደበኛ መግለጫው ከዲፕሎማሲ አንጻር የተከናወኑ አንኳር ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ ሰጥቷል።

መግለጫውን የሰጡት የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ፣ በሳምንቱ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በኮትዲቯር፣ በጋቦንና በአንጎላ የተሳካ የዲፕሎማሲ ስራ ማከናወናቸውን አንስተዋል።

በጉብኝቱ ፕሬዚዳንቷ ለሶስቱ አገራት መሪዎች የኢትዮጵያን እውነታ አስረድተው፣ አገራቱም ከኢትዮጵያ ጎን መሆናቸውን አረጋግጠዋል ነው ያሉት።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ፣ የቱርክ አፍሪካ ጉባኤ ተሳትፎ እና የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የደቡብ ሱዳን ጉብኝትም ውጤታማ እንደነበር አስረድተዋል።

አምባሳደር ዲና በመግለጫቸው ምዕራባውያን የመገናኛ ብዙሃን አሸባሪው ሕወሓት በአማራ እና አፋር ክልሎች በወረራ በቆየባቸው አካባቢዎች በንፁሃን ላይ የፈፀመውን አሰቃቂ ግድያና የንብረት ውድመት መዘገብ አልፈለጉም ብለዋል።

አሸባሪው ቡድን በወረራ ይዟቸው የነበሩ አካባቢዎች በሰራዊቱ ነጻ እስከሚወጡ ድረስ ያልፈፀመው ወንጀል ያላደረሰው ውድመት እንደሌለ አንስተዋል።

ይሁን እንጂ አንዳንድ የምእራቡ ዓለም ሚዲያዎች በኢትዮጵያ ላይ የሃሰት መረጃ ያሰራጩትን ያክል ለእውነታና ሰብአዊነት ደንታ ቢስ ሆነው ታይተዋል ብለዋል።

የመገናኛ ብዙሃኑ አጀንዳ የሽብር ቡድኑን የማዳን እንጂ ሰብአዊነትንና የተፈፀመውን እውነታ የማሳወቅ ፍላጎት አንደሌላቸው ማሳያ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ምክክር ኮሚሽን አዋጅ ከመዘጋጀቱ ጋር ተያይዞ አንዳንዶች ጉዳዩን መንግስት ከአሸባሪው ህወሃት ጋር የሚደረግ ድርድር በማስመሰል ህዝብ ለማደናገር እየጣሩ መሆኑን ጠቅሰዋል።

''ሁሉን አቀፍ ውይይት ያስፈልገው ኢትዮጵያ ከግጭት አዙሪት መውጣት ያቃታት ለምን እንደሆን በሕዝብ ደረጃ ለመወያየት ነው'' ብለዋል።

ከዚህ ባለፈ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት የተፈረጀው  አሸባሪው ህወሃት የከፈተው ጦርነት ጋር መያያዙ ተገቢነት የለውም ነው ያሉት።

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ባደረገችው ጥሪ መሰረት በርካታ ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያኖችንና ወዳጆችን ለመቀበል ዝግጅቱ እየተጠናቀቀ መሆኑን ገልጸዋል።

ከሁሉም በላይ ዳያስፖራው የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ የመደገፍና በተለያዩ ኢንቨስትመንት አማራጮች መሳተፍ እንደሚችል መረዳት ያስፈልጋል ብለዋል።

የአፍሪካ የሰላምና ጸጥታ ምክር ቤት ስብሰባ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰብስባቢነት መካሄዱንና ጠቃሚ ሀሳቦች የተንሸራሸሩበት እንደነበረም አንስተዋል።

በሳምንቱ በአዲስ አበባ ተቀማጭነታቸውን ላደረጉ የተለያዩ አገራት አምባሳደሮች በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ዙሪያ ገለጻ መደረጉም ተነስቷል።

አሸባሪው ሕወሓት በአፋርና አማራ ክልሎች በጤናና ትምህርት ላይ ያደረሰውን ውድመት አስመልክቶ የዓለም ጤና ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይና የዩኔስኮ ተወካዮች ዝምታን መምረጣቸው አሳዛኝ እንደሆነ ተገልጾላቸዋልም ብለዋል አምባሳደር ዲና።

በሳምንቱ የኤምባሲዎች እንቅስቃሴና የዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ ውጤታማ ስራዎችን የተመለከተ ማብራሪያም ተሰጥቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም