በባሌ ዞን ከ19 ሺህ በላይ ወጣቶች የስራ እድል ተመቻቸላቸው

75

ጎባ፤ ታህሳስ 14/2014(ኢዜአ) በተያዘው የበጀት ዓመት ያለፉት አምስት ወራት ከ19 ሺህ600 ለሚበልጡ ወጣቶች የስራ እድል የተመቻቸላቸው መሆኑን የባሌ ዞን የስራ እድል ፈጠራና ክህሎት ጽህፈት ቤት አሰታወቀ።

ለወጣቶቹ ከተመቻቸው የስራ እድል ውስጥ ንግድ፣ አገልግሎት፣ ግብርና፣ ማኑፋክቸሪንግ፣ ግንባታ፣ የእንስሳት እርባታና ማድለብ እና የተፈጥሮ ሀብት ልማት ጥበቃ ይገኙበታል።

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ጫልችሳ ዘውዴ በተለይ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ለወጣቶቹ 123 የመስሪያና መሸጫ ቦታዎችን እንዲሁም  ለከብት ማደለብ ጨምሮ ከ800 ሄክታር በላይ መሬት ለተለያዩ የግብርናና የአካባቢ ጥበቃ ልማት ስራዎች ተሰጥቷል።

ወጣቶቹ የመነሻ ካፒታል እጥረት እንዳያጋጥማቸው 10 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር ብድር ማቅረብ መቻሉንም አመልክተዋል።

በዞኑ የስራ እድል ከተመቻቸላቸውወጣቶች ውስጥም 3 ሺህ የሚሆኑት ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተመረቁ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

በማህበራት ለተደራጁ ወጣቶች በአካባቢው ከሚገኙ የግልና መንግስታዊ ተቋማት እንዲሁም እርስ በርሳቸው የ100 ሚሊዮን ብር የገበያ ትስስር ለመፍጠር መታቀዱን የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ ተናግረዋል፡፡

“እስከ በጀት ዓመቱ መጨረሻም ከ37 ሺህ በላይ ወጣቶች ተደራጅተው ወደ ስራ እንዲገቡ ይደረጋል ብለዋል።

አብዮት መንግስቱ በአጋርፋ ወረዳ አሊ ቀበሌ የስራ እድሉ ከተመቻቸላቸው ወጣቶች መካከል አንዱ ሲሆን፤ ከሌሎች ወጣቶች ጋር በመደራጀት ከመንግስት የተመቻቸላቸውን የብድር ገንዘብ በመጠቀም በግብርና ልማት ላይ መሰማራታቸውን ለኢዜአ ተናግሯል።

በዚህም በመኸሩ ወቅት ከአካባቢያቸው ትምህርት ቤት በኮንትራት ባገኙት  የእርሻ ማሳ ላይ የፓስታና ማካሮኒ ስንዴ እያለሙ መሆናቸውን አመልክቷል፡፡

የተሻሻሉ የግብርና አሰራሮችን ተጠቅመው በማልማታቸው ከአንድ ሄክታር እስከ 70 ኩንታል ምርት እንደሚጠብቁ  ነው የገለጸው፡፡

አምስት ሆነን ተደራጅተን በመንገድና ድልድይ ስራ በመሰማራት ማህበረሰባችንን በተማርነው ሙያ ከማገልገላችን በተጓዳኝ በምናገኘው ገቢም ውጤታማ እየሆንን መጥተናል ያለው ደግሞ ሌላው የወረዳው ነዋሪ ወጣት ኢብሳ ሁሴን ነው፡፡

የመንገድና ድልድይ ስራ ጅማሮው መልካም መሆኑን የጠቆመው ወጣቱ፤ በተመቻቸላቸው የስራ እድል ከቤተሰብ ጠባቂነት ተላቀው አሁን ላይ  አንድ ሚሊዮን ብር የሚጠጋ  ገንዘበ በባንክ መቆጠብ እንደቻሉ ተናግሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም